ውህደቱ እኩል ተሳታፊነትን የሚያረጋግጥ ነው --- የጋምቤላ ነዋሪዎች

57
ህዳር 9 ቀን 2012 የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ያደረገው ውህደት ሁሉም ዜጋ በአገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆን እድል የሚሰጥ መሆኑን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ ያፀደቀው ውህደት ሁሉም ዜጎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እድል ይሰጣል፡፡ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ማቲያ ኡችች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የሚወጡ ህግና ደንቦች ሁሉንም ዜጎች ያካተተ ሳይሆን የተወሰኑ አካላት ባወጡትና ባስተላለፉት ውሳኔ ለመመራት የሚገደዱበት ሁኔታ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ጋምቤላን ጨምሮ አጋር ክልሎች በአገሪቱ የሚወሰኑ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ ሳይሆኑ ከላይ የመጣውን አስፈጻሚ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ እናም አሁን የተደረገው ውህደት እነዚህን ችግሮች በመፍታት በአገሪቱ ጉዳይ ላይ ሁሉም ዜጋ በእኩል ተሳታፊ የሚሆንበትን እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም የነበረው ህገ መንግስቱን መሰረት ያላደረገና የበይና ተመልካችነት ሁኔታን የፈጠረ እንደነበረ አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም የአሁኑ ውሳኔ ይህን ችግር ከመፍታቱም ባለፈ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት አንድነትን ከማጠናከር አንጻርም የራሱ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ውሳኔው የክልሉ ህዝብ ባለፉት ዓመታት በአገራዊ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ሲጠይቁ የነበረውን ምላሽ የሚሰጥ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዶት ኮዝ ናቸው፡፡ ከዚህም ባለፈ የተደረገው ውህደት በአገሪቱ ፖለቲካዊ አደረጃጀት ላይ የክልሉ ተሳትፎ ሊያሳድግ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ጥበቡ በቀለ በበኩላቸው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያጸደቀው የፓርቲ ውህደት ሁሉም ዜጋ በይገባኛል ስሜት ለአገሪቱ እድገትና ብልጽግና እንዲሰራ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡በተለይም ውህደቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን የውሳኔ ሰጪነትና ተቀባይነት ስርዓት በማስቀረት የሚወጡ ህግና ደንቦችን ሁሉም በጋራ የሚወስኑበት እድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል ፡፡ በተላለፈው ውሳኔ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ውህደቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ኡቡል ኡቻር ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህ ውሳኔ ስኬታማ እንዲሆን በቀጣይ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አንድ ፓርቲ ለመመስረት ያጸደቀው ውሳኔ በተለይም ለአጋር ድርጅቶች የአመታት ጥያቄን የመለሰ ከመሆኑም ባለፈ ለአገራዊ አንድነትም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም