የአፋርና ኢሳን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ

66
ሰመራ ኢዜአ ህዳር 09/2012 የአፋርና ኢሳ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡስማን መሀመድ ገለጹ። በገዋኔ ወረዳ እንድፍኦ ቀበሌ በአፋርና ኢሳ ህዝቦች መካከል ላለፉት አራት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው የሰላም ኮንፈረንስ ዛሬ ተጠናቀቀ። በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ እንደተናገሩት ባለፈው አንድ ዓመት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረው አለመግባባት ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሰት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ሲሰራ ቆይቷል። በወቅቱም በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ከመድረሱም በላይ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድርግ የሚችሉ የልማት ስራዎች ላይ እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል። በቀጣይ የክልሉ መንግስት በአካባቢው የሚኖሪ የአፋርና ኢሳ ህዝቦች ግንኙነትን  በማጠናከር ያለባቸውን የልማት ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። “በመካከላቸው ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲሰፍን ብሎም የጋራ ስፖርት፤ ልማትና የንግድ ትስስርቸው እንዲጎለበት የክልሉ መንግሰት ይሰራል” ብለዋል የእንድፍኦ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ በሪ አርዴ በሰጡት አስተያየት ከምንም በላይ በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል ሰላም እንዲሰፍን  መግባባት ላይ በመደረሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ተሳስተው ወደ ግጭት የገቡ የህብረተሰቡ አካላት በመምከርና በማስተማር ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ የሚሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። ህብረተሰቡም ግጭት ውስጥ ለመግባት የሚፈልጉ አካላትን ለይቶ ለህግ አሳልፎ በመስጠት ሰላሙ እንዲጠበቅ ጠቁመዋል። ሌላው የኮንፍረንሱ ተሳታፊ የኃይማኖት አባት ሼክ ኢልሚ ኡስማን በበኩላቸው ሁለቱ ህዝቦች ተመሳሳይ ባህል የሚጋሩ ወንድማማች እንጂ ለመጎዳዳት የሚያበቃ ምንም ምክንያት እንደሌላቸው ገልጸዋል። የሰውን ህይወት ማጥፋት ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ በመሆኑ ሁሉም ካለፈው ስህተት በመማር በጋራ ተባብረው ለሰላምና ልማት እንዲቆሙ መክረዋል። የአፋርና ኢሳ ማህብረሰብ ወንድማማችነት፣ አብሮነት እና ሰላም እንዲጎለበት የኃይማኖት አባቶች ማስተማር እንዳለባቸው ያመለከቱት ደግሞ ሼክ አሊ አደም ናቸው። በኮንፈረንሱ ከ300 በላይ የሁለቱ ህዝቦች የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም