የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ድርጅት በስድስት የአዲስ አበባ አዋሳኝ ከተሞች አገልግሎት መስጠት ጀመረ

80

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 9 /2012 የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ድርጅት ወደ ቡራዩ፣ ሆለታ፣ ጫንጮ፣ ሰበታ፣ ሰንዳፋና ሱሉልታ ከተሞች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

መዳረሻዎቹ አምስት መስመሮች ሲኖራቸው ሱልሉታና ጫንጮ በአንድ መስመር ይጠቃለላሉ ብሏል።

በአገልግሎቱ 500 የመንግስት ሠራተኞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ድርጅቱ ገልጿል።

ይህ አገልግሎቱ በሙከራ ደረጃ በቢሸፍቱ የጀመረውን አገልግሎት ለማስፋት ያለመ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልነበሩ የመንግስት ሠራተኞች ያቀረቡትን ጥያቄም ይመልሳል ብለዋል።

ሚኒስትሯ አያይዘውም የመንግሥት ሠራተኞች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ህብረተሰቡን በንቃት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።

በአገልግሎቱ የፌዴራልና የአዲስ አበባ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተቋሙ የኦፕሬሽን አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ተዘራ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የአገልግሎቱ መጀመር ሠራተኞች ስራቸውን በአግባቡ እንዲከውኑ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን ወጪያቸውን፣ ጊዜያቸውንና እንግልታቸውንም ይቀንሳል ብለዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎቱ በሚያልፍባቸው ከተሞች የሚታየውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ከመቀነሱ ባሻገር ሠራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ በሠዓታቸው እንዲገኙም ያስችላል።

ሠራተኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በከተሞቹ ነዋሪ መሆናቸውን የሚገልጽ መታወቂያ መያዝ ግዴታቸው ነው ተብሏል።

ለተጠቃሚዎቹ ልዩ መታወቂያ እንደሚዘጋጅም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በ391 አውቶቡሶች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም