ተግባራዊ በሆነው የማሻሻያ ለውጥ በርካታ የክስ መዝገቦች እልባት ያገኛሉ - አቶ ተስፋዬ ንዋይ

54

ህዳር 9 ቀን 2012 በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ በተደረገው የማሻሻያ ለውጥ በተያዘው ዓመት ከ217 ሺህ በላይ የክስ መዝገቦች እልባት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ።

በተያዘው ዓመት በፌዴራል ደረጃ ባሉ ሁሉም ፍርድ ቤቶች ከሚቀርቡ 263 ሺህ የክስ መዝገቦች 217 ሺህ 232 እልባት እንያገኙ ይጠበቃል።

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በፍርድ ቤቶች የሚታየውን የቀጠሮ መጓተት ችግር ለመፍታት የማሻሻያ ለውጥ ተተግብሯል።

ተግባራዊ በሆነው የማሻሻያ ለውጥ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ከተዘረጉ አሰራሮች መካከል የጉዳዮች ፍሰት አመራርና የአስተዳደር ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ የጉዳዮች ፍሰት አመራርና አስተዳደር ስራዎች ዋና ተግባር የተከፈቱ የክስ መዝገቦች በቀጠሮ ብዛት መጓተት እንዳይከሰት ማድረግ ነው።

የቀጠሮ መብዛት የሚታይባቸውን መዝገቦች ምክንያታቸውን መፈተሽ ጭምር መሆኑንም አስረድተዋል።

የፍርድ ቤት መር የአስማሚነት ስራ በማሻሻያ ለውጡ ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተከራካሪዎችን የማሸማገል አቅጣጫን የሚከተል አሰራር መሆኑን ገልጸዋል።

''የማሻሻያ ለውጡ ዳኞች ህግን፣ ማስረጃና ፍሬ ነገርን መሠረት አድርገው ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የሚያስችል ነው'' ብለዋል።

ተግባራዊ የተደረገው የማሻሻያ ለውጥ በአጭር ጊዜ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትህ ስርዓት ላይ ለውጥ ማምጣቱን ባለጉዳዮችን መሰረት አድርጎ በተካሄደ ጥናት መረጋገጡንም አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክሊት ይመስል በተያዘው ዓመት በፍርድ ቤቶች ከሚቀርቡ የክስ መዝገቦች 28 ሺህ የሚሆኑት በከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚታዩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኀብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የፍትህ መጓተት ቅሬታዎችን የሚፈታ የማሻሻያ ለውጥ ተግባራዊ መደረጉን በመጥቀስ።

ፍርድ ቤቶች በሰው ህይወት፣ ነፃነትና ንብረት ላይ ውሳኔ የሚሰጡ በመሆናቸው ኀብረተሰቡ በእውነት ላይ የተመሰረተና በማስረጃ የተደገፈ ክስ ይዞ መቅረብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራትን ለማገዝ ኀብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ግድፈቶችን ለፍርድ ቤቶች እንዲያሳውቅም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም