በአዲስ አበባ የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ተከላ ተጀመረ

76

ህዳር 9 ቀን 2012 በአዲስ አበባ በተመረጡ አካባቢዎች የአየር ብክለት መጠንን በመለካት መረጃ የሚሰጡ መሳሪያዎች ተከላ ዛሬ ተጀምሯል።

በአስር አካባቢዎች የሚተከሉት መሳሪያዎች የመዲናዋን የአየር ብክለት መጠን በመለካት መቆጣጠር እንደሚያስችሉ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ምክትል ኮሚሽነር ኢንጂነር ጉተማ ሞረዳ ተናግረዋል።

መሳሪያዎቹ የሚተከሉት የከተማዋን የአየር ጥራት ማኔጅመንት ዕቅድ ለመተግበር በከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ዘርፍ የገንዘብ ድጋፍ  ነው።

ሜክሲኮ፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ቆሼ ሰፈር፣ መርካቶ፣ ቦሌ ለሚና ኢንዱስትሪዎች በብዛት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ለመሳሪያዎቹ ተከላ ተመርጠዋል።

ዛሬና ነገ አምስት መሳሪያዎች የሚተከሉ ሲሆን የቀሪዎቹም በቀጣይ ይከናወናል ተብሏል።

መሳሪያዎቹ በከባቢ አየር ውስጥ ያለን ብናኝ፣ የኦክስጅን፣ የካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ፣ የናይትሮጅን ዳይ ኦክሳይድ እና የሌሎች ጋዞችን መረጃዎች ያሳውቃሉ።

ከመሳሪያዎቹ የሚገኘው መረጃም የአየር ብክለትን መቆጣጠር የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ለመቅረጽ ያገለግላል።

የኢትዮጵያ የአየር ብክለት መጠን ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ብዙም ችግር እንደሌለውና መሳሪያዎቹ በአረንጓዴ ልማቱ የመጣን ለውጥ ለመመዘን ጭምር እንደሚረዱ ኢንጂነር ጉተማ ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ የአየር መረጃውን በመጠቀም ስፖርታዊና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በማድረግ ጤናውን እንዲጠብቅም ያስችለዋል ነው ያሉት።

መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የከተማዋን አየር ብክለት መቀነስ የሚያስችሉ ከተሽከርካሪ ነፃ ቀን እንዲኖር፤ በብዛት ጭስ የሚለቁ ኢንዱስትሪዎችን ለመቆጣጠርም ይቻላል ብለዋል።

ይህን መነሻ በማድረግ ፕሮግራሙ የአገሪቷ አንድ ሶስተኛ ተሽከርካሪ ብዛትና የኢንዱስትሪ ባለቤት በሆነችው አዲስ አበባ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

መሳሪያዎቹ በፀሐይና በኤሌክትሪክ ኃይል መስራታቸው ለአጠቃቀም ምቹ ያደረጋቸው ሲሆን መረጃ ለማስተላለፍ የሚያግዝ የሞባይል መተግበሪያም ተዘጋጅቶላቸዋል።

የአየር ብክለት መለኪያ መሳሪያዎቹ በመንግስት ደረጃ ሲገጠሙ የመጀመሪያ ቢሆኑም በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ  ቀደም ብሎ የሚጠቀምበት የብክለት መቆጣጠሪያ እንዳለው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም