በሊጉ ውድድር ችግሮች እንዳይከሰቱ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል - የስፖርት ባለሙያዎች

120

ኅዳር 09 ቀን 2012 የኢትዮጵያ እግር ኳስ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በተያዘው ወር እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

የስፖርቱ ባለሙያዎችም የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች ለማካሄድ የሚመለከታቸው አካላት አስቀድመው የቤት ስራቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት የሚመለከታቸው አካላት የቤት ስራቸውን በአግባቡ ካልተወጡ አገራዊ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት መመህር አቶ የማነ ጎሳዬ እግር ኳስ በባህሪው በርካታ ሰዎችን የሚያሰባስብና ስሜታዊ የሚያደርግ ስፖርት ነው ይላሉ።

እናም ይህን ስፖርት የተለያየ ዓላማ ያላቸው አካላት በአሉታዊ መልኩ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል በጥንቃቄ መምራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በአግባቡ ከተመራ ሕዝብ ለማስተሳሰር፣ የአገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍና ሌሎች ጥቅሞች እንዳሉት ጠቅሰው በጥንቃቄ ካልተመራ፣ በፌዴሬሽኑም ይሁን በካፍ ወይንም በፊፋ የተቀመጡ መመሪያዎች በትክክል ካልተተገበሩ ግን ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

እነዚህን ችግርች ለመቀነስ በዋናነት እርምጃ መውሰድ፤ የእግር ኳስ አመራሮችና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በማካተት መነጋገርና ውይይቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ይህ የሚያስፈልገው በእግር ኳሱ የሚታዩ ችግሮች እንደ አገር ያለው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ነጸብራቅ በመሆናቸው ነው ሲሉም አክለዋል።

ክለቦችን በኃላፊነት የመሩትና በእግር ኳስ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያቀርቡት አቶ ገዛኸኝ ወልዴም አሁን ያለው የእግር ኳስ አደረጃጀት በየቦታው የሚስተዋሉ ችግሮችን ሊያባብስ ስለሚችል ቢቀየር የተሻለ እንደሆነ አስተያየት ሰጥተዋል።

ይህ መደረጉ የፀጥታ ችግሩን ለማቃለልና እግር ኳሱንም ለማሳደግ የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል።

አቶ ገዛኸኝ እንደ አማራጭ ያቀረቡት ሀሳብ ጨዋታዎችን በዞን ወይም በክልል ማካሄድ የክለቦችን ወጪ ለመቀነስና ታዳጊዎችንም ለማፍራት ዕድል ይፈጥራል የሚል ነው።

ክለቦች አቅም ከፈጠሩ በኋላ እየተዟዟሩ መጫወቱ ቢችሉ የተሻለ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ አካላት በአገሪቷ ይካሄዳሉ በሚባሉ ሁነቶች የሚኖራቸውን ቅሬታ በእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ አስቀድሞ መጠንቀቅና መፍትሄ ማበጀት ይገባል ይላሉ።

ባለፈው ዓመት በእግር ኳሱ የፕሪሚየር ሊግ አደረጀጃት ዙሪያ ያነጋገርናቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ቡናና ሌሎች የክለብ አመራሮች አደረጃጀቱን በክልል ወይም በዞን በማድረግ በእግር ኳሱ የሚታየውን የጸጥታ ችግር መቀነስ እንደሚቻል፣ እግር ኳሱን ለማሳደግም የተሻለ አማራጭ ነው የሚሉትን ሃሳቦች ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም