ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚን ማጠናከር ላይ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር እየሰራች ነው

72

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 9 /2012 ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚን ማጠናከር ላይ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር እየሰራች መሆኗ ተገለጸ። 8ኛው የአፍሪካ አገራት የአገር ውስጥ ቦንድ የፋይናንስ ዘርፍ ልማት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር 2008 በባንኩ ይፋ በሆነው የአፍሪካ የፋይናንስ ገበያ ኢኒሼቲቭ ላይ ያተኮረውን አውደ ጥናት የአፍሪካ ልማት ባንክ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በተመባበር አዘጋጅቶታል።

ባለድርሻ አካላት፣ የተለያዩ አገራት ተወካዮችና ባለሙያዎችም እየተሳተፉበት ነው።

የኢኒሼቲቩ ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካ አገራት ከውጭ አገራት ተጽዕኖ እንዲላቀቁ ማገዝ ሲሆን ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድም የአገር ውስጥ የቦንድ ገበያ እንዲስፋፋ እየሰራ ነው ተብሏል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢኒሼቲቩን ተግባራዊ እያደረገ ያለው በሁለት መንገድ መሆኑን ጠቁሞ የአፍሪካ የፋይናንስ ገበያ መረጃ ቋትና የአፍሪካ የአገር ውስጥ ቦንድ ፈንድ ተጠቃሽ ናቸው።

የአውደ ጥናቱ ዓላማም ባለፉት ዓመታት በኢኒሼቲቩ የተሰሩ ስራዎችን በመዳሰስ የአፍሪካ አገራት ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግና የአገር ውስጥ የፋይናንስ ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ ማገዝ ነው።

የብሔራዊ ልማት ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት አቶ ፈቃዱ ድጋፌ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚ ላይ መስራቷ ለዘላቂ እድገት ወሳኝ ሚና አለው።

የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱና ቁልፉ ጉዳይ የአገር ውስጥ ቦንድ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያም በዚህ አውደ ጥናት መሳተፏ በርካታ ተሞክሮ እንድትቀስም ያስችላታል ብለዋል።

''የአፍሪካ ልማት ባንክ በአገር ውስጥ ቦንድ ገበያ ዙሪያ አማካሪ መድቦ ከእኛ ጋር እየሰራ ነው'' ያሉት ምክትል ገዥው ጥናት ከተደረገ በኋላ የቦንድ ሽያጭ ስርዓት እንደሚዘረጋም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ፈቃዱ ገለጻ የቦንድ ገበያ ካፒታልን ማሳደግ ለአገሪቷ ኢኮኖሚ መነቃቃት ወሳኝ ድርሻ አለው።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የካፒታል ገበያ ልማት ክፍል ኃላፊ ኢማኑኤል ዲያራ በበኩላቸው ባንኩ የአፍሪካ አገራት የፋይናንስ ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ማተኮሩን ገልጸዋል።

በተለያዩ አገራት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ከአቅም ግንባታ ስራዎች መካከል እንደሚገኙበት ጠቁመው የአፍሪካ ፋይናንስ ገበያ ኢኒሼቲቭ አንዱ መሆኑን አክለዋል።

አውደ ጥናቱ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም