የተርባይኖች መቀነስ የሕዳሴ ግድቡ በሚያመነጨው የኃይል መጠን ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም

28
ኢዜአ  ህዳር 8/2012  የተርባይኖች መቀነስ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚያመነጨው የኃይል መጠን ላይ የሚፈጥረው ለውጥ እንደሌለ የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ተቆጣጣሪና ሜካኒካል መሐንዲስ ኢንጂነር አብዱ ይብሬ ገለጹ። በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል እንዲያመነጩ ሊተከሉ ከታቀዱት 16 ተርባይኖች መካከል በባለሙያዎች ምክረ ሃሳብና ውሳኔ ሶስቱ እንዲቀነሱ መወሰኑ ይታወቃል። በሦስቱ ተርባይኖች መቀነስ ግድቡ በሚያመነጨው ኃይል መጠን ላይ የሚኖረውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አስመልክቶ ኢዜአ የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ተቆጣጣሪና ሜካኒካል መሐንዲስ ኢንጂነር አብዱ ይብሬን አነጋግሯል። ኢንጂነር አብዱ ''የተርባይኖቹ ቁጥር መቀነስ ግድቡ ያመነጫል ተብሎ የሚገመተውን የመጨረሻ የኃይል አቅም ከ6 ሺህ 350 ወደ 5 ሺህ 150 ሜጋዋት ይቀንሰዋል እንጂ የሚመረተው የኃይል መጠን ላይ ምንም የሚፈጥረው ለውጥ የለም'' ይላሉ። ኃይል ማመንጨት ማለት በተቀመጠ የጊዜ ገደብ አንድ ተርባይን የሚያመርተው ኃይል እንደሆነም ኢንጅነሩ አብራርተዋል። እያንዳንዳቸው 13ቱ ተርባይኖች ኃይል የሚያመርቱበትን ጊዜ ከፍ በማድረግ ከዚህ በፊት 16ቱ ተርባይኖች ሊያመርቱ ከሚችሉት ኃይል ጋር እኩል እንዲሆኑ እንደሚደረግ ኢንጅነር አብዱ አስረድተዋል። በኃይል (ኢነርጂ) ጽንሰ ሀሳብ የሃይል ማመንጨት አቅም ሳይሆን ገንዘብ የሚያስገኘው የሚመረተው የኃይል መጠን እንደሆነም እንጂነሩ ገልጸዋል። "በ16 ተርባይኖች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ 6 ሺህ 350 ሜጋ ዋት የማመንጨት እቅድ ከኃይል ማመንጨት አቅም አኳያ የማይቻል ነው" ሲሉ ነው ኢንጂነሩ ያስረዱት። በዚህም ምክንያት የኃይል አቅም በመቀነስና ተርባይኖቹ ኃይል የሚያመርቱበትን ሠዓት ከፍ በማድረግ የሚፈለገውን የኃይል መጠን ማምረት እንደሚቻል አብራርተዋል። የተርባይኖቹን ቁጥር ወደ 13 መቀነስ ተቀናሾቹን ተርባይኖች ለመትከል የሚፈጀውን ጊዜ፣ አላስፈላጊ የኢንቨስትመንት ወጪና ከተርባይኖች መብዛት ጋር በተያያዘ ለጥገና የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ አንጻር ውሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል። በአጠቃላይ የተርባይኖች መቀነስ ጊዜን በበቂና ውጤታማ መልኩ በመጠቀም ኃይል ለማምረት እንደሚያስችል አክለዋል። የኃይል አቅም በሜጋ ዋት የሚገለጽ ሲሆን፤ የኃይል ማምረት በጊጋዋት ሀወር የሚቀመጥ ነው። 13ቱ ተርባይኖች ከዚህ በፊት በ16 ተርባይኖች ለማምረት የታቀደውን 15 ሺህ 760 ጊጋዋት ሀወር ማምረት እንደሚቻል ኢንጂነር አብዱ ይብሬ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም