የቋራ ወረዳ ነዋሪዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻቸውን እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

47

ጎንደር ህዳር 9 ቀን 2012 መንግስት ለዓመታት የዘለቀውን የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን እንዲፈታላቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን የቋራ ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ ወረዳውን ከሁለት አቅጣጫ የሚያገናኙ መንገዶችን ለመገንባት በፌደራል መንግስት በጀት ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በወረዳው የገለጉ ከተማ ነዋሪ አቶ ደረጀ አስማማው እንደተናገሩት ወረዳው ከፍተኛ የሰሊጥ፣ ጥጥ፣ የጥራጥሬ ሰብሎችና የእንስሳት ሀብት መገኛ ቢሆንም በመንገድ ችግር ምክንያት ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ብለዋል ።

"በተለይ ከገንዳውኃ ቋራ ያለውን መንገድ ህዝቡ እንዲሰራለት ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ቢያቀርብም እስከ አሁን ድረስ መልስ አልተገኘለትም" ያሉት አርሶ አደሩ በተለይም በክረምት ወራት የባሰ ስለሚበላሽ ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ጥጋቡ ይርሳው በበኩላቸው ወረዳው ለኢንቨስትመንት ምቹ ቢሆንም የመንገድና የመብራት ችግር በመኖሩ ባለሃብቶች መጥተው ኢንቨስት እንዳያደርጉ አንቅፋት መፍጠሩን ገልፀዋል ።

"በወረዳው የሚስተዋለው የመንገድና የመብራት ችግር ቢቀረፍ ባለሃብቶችን በመሳብ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ይቻል ነበር" የሚል ሃሳብ አላቸው ።

"በመንገድ ችግር ምክንያት ከተማዋ እንዳታድግና በዙሪያዋ የምንገናኝ አርሶ አደሮች በምናመርተው ልክ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል" ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አቶ ቢያዝን መልካሙ ናቸው፡፡

ወረዳው የተሟላ የመሰረተ ልማት የሌለው በመሆኑም የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ መጥተው እንዳይጎበኙ እንቅፋት ሆኖባቸዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

መንግስት የህዝቡን ጥያቄና የወረዳውን ሰፊ ሀብት ከግምት ውስጥ በማስገባት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በአግባቡና በተቻለ ፍጥነት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ሁኔታውን አስመልክተው እንደተናገሩት ወረዳውን ከሁለት አቅጣጫ የሚያገናኝ መንገድ ለማስገንባት በፌደራል መንግስት በጀት ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በዚህ ዓመት ግንባታቸው የሚጀመሩት ሁለቱ የአስፋልት መንገዶች ከገንዳውኃና ሻሁራ በመነሳት መዳረሻቸውን የወረዳው ዋና ከተማ ገለጉ የሚያደርጉ ናቸው ።

የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ የወረዳው ነዋሪዎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድግላቸው ከዋና አስተዳዳሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም