የሰላም መደፍረስ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ጫና እንዳይፈጥር እየተሰራ ነው

50
ኢዜአ ሕዳር 09 / 202 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ አለመረጋጋቶች በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ጫና እንዳያሳድሩ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ባለሃብቶች በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ በማጤን መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱም ሰላምን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። በሚኒስቴሩ የውጭ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ጄነራል ዳዊት አፈወርቅ ለኢዜአ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉት የሰላም እጦት ችግር በኢንቨስትመንቱ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ እየተሰራ ነው። ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑንም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች መረጃዎችን እያደረስን ነው ብለዋል። በተለይም የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በታዳሽ ሃይልና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ሰፊ እድል ይዞ መምጣቱንም እንዲሁ። በአገሪቷ ባለው ለውጥ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ቢኖሩም የአጭር ጊዜ ክስተትና ወደ አስተማማኝ ሰላም እንዲያመራ እየተሰራ መሆኑን ለተለያዩ የአለም አገራት ባለሃብቶች መረጃ እያደረስን ነው ብለዋል። እንደ ዳይሬክተር ጄነራሉ ገለጻ ይኸን የማስተዋወቁን ስራም በኤምባሲዎች፣ በድረ-ገጾች፣ በኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሃን፣ በህትመትና በሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀምበኩል እየተሰራ ነው ብለዋል። የማስተዋወቅ ስራ ብቻም ሳይሆን በኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ መጥተው እንዲያዩም የማግባባት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም በተለያዩ የአለም አገሮች ያሉ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ በማየት ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ነውም ብለዋል። ከነዚህም የሳዑድ ዓረብያ፣ ኩዌትና ደቡብ ኮርያን ባለሃብቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ከኩዌት ባለሃብቶች ጋር በሽርክና አብረው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር በቀጣይ ወር ወደ እዚያው ያቀናሉም ብለዋል። በስጋ ምርት፣ በቡና ማቀነባባሪያ፣ በቅባት እህሎች ላይ በኢትዮጵያ ያለውን እድል የሚያስተዋውቁ እንደሚሆንም ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከሳዑድ ዓረቢያና ደቡብ ኮርያ ደግሞ በጨርቃ ጨርቅና ግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ያለውን ሁኔታ በተጨባጭ ለማየት እንደሚመጡም ነው የገለጹት። ባለሃብቶች ወደ ስራ አንዲገቡ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሰላም ማስፈን እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ባለሃብቶች ይዘው የሚመጡትን፣ ገንዘብና የእውቀት እንዲሁም ሊፈጥሩ የሚችሉትን የስራ እድል ለመጠቀም በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው የሰላም ሁኔታ መሻሻል እንዳለበትም በማከል።                                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም