ዲያስፖራውን በልማት ለማሳተፍ አገራዊ ሠላም ማስፈን ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል

84
ኢዜአ ሕዳር 09 / 202 ዓ.ም. ዲያስፖራው በልማት ስራዎች በስፋት እንዲሳተፍ በአገር ውስጥ አስተማማኝ ሠላም ማስፈን የመጀመሪያ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር ገለጸ። ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ በእውቀትና ባላቸው አቅም አገራቸውን እንዲያገለግሉ በተለያየ ጊዜ በመንግስት ጥሪ ይደረግላቸዋል። ዲያስፖራውም ጥሪውን ተቀብሎ በአገር ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የልማት ስራዎች ያለው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ባለው አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ የሠላም ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ዲያስፖራው በሚጠበቀው ልክ ተሳትፎ እያደረገ አለመሆኑ ነው የተገለጸው። የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአገሪቷ የሠላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ መሆን ዲያስፖራው በልማትና በኢንቨስትመንት እንዳይሳተፍ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል። 'ሠላምን በመዘመር ብቻ ልናሰፍን አንችልም' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሠላምን ለማረጋገጥ ከሁሉም ዜጎች የተግባር ስራ ይጠበቃል ነው ያሉት። ''ሠላምን በመመኘት ከአላስፈላጊ ንግግር፣ ከምንሰራቸው አፍራሽ ተልዕኮዎችና ተግባራት በመቆጠብ የራሳችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባል'' ብለዋል። ዲያስፖራው በአገሩ ጠንካራ እምነት እንዳለው በመግለጽም የልማትና የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እውቀትና ጊዜውን በመጠቀም መዋዕለ ነዋዩን እንዲያፈስ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም መንግስት ከዜጎቹ ጋር በመሆን የተረጋጋችና በኢኮኖሚ የበለጸገች አገር ለመገንባት ሠላም ለማስፈን ስራ ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባም አመልክተዋል። የኦሮሚያ ክልል ዲያስፖራ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ አብዳ ጀማልአብዳ እና የአማራ ክልል ዲያስፖራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሃብታሙ አዱኛ ዲያስፖራው በክልሎቹ ልማት እንዲሳተፍ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ዲያስፖራው የአገሩንም ሠላም ለማስጠበቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ውጭ አገር ካሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም