ቢሮው የተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ልማት ሥራዎችን ከስዊድን ዘላቂ ልማት ማህበር ጋር በጋራ ለመስራት ተፈራረመ

66
ኢዜአ ህዳር 09/2012 ዓ.ም በትግራይ የሚካሄዱ የተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃ ልማት ስራዎችን ከስዊድን ዘላቂ ልማት ማህበር ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተደረገ፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቦ እና  የልማት ማህበሩ ፕሬዚዳንት ሚስተር ተርብጆርን ላህቲ ናቸው፡፡ በስምምነቱ መሰረት በትግራይ ክልል በየዓመቱ ለሚካሄዱ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የስዊድን ልማት ማህበር በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የልማት ማህበሩ ፕሬዚዳንት ሚስተር ተርብጆርን ላህቲ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ተፈጥሮን ማዕከል አድረገው በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ላይ ማህበሩ ልምዱን ከማጋራት ባለፈ ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቦ በበኩላቸው፣ በክልሉ ለብዙ ዓመታት ተፈጥሮን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ "በክልሉ ባለው ልምድና ተሞክሮ የሌሎች አካላት ድጋፍ ቢጨመርበት ስራውን የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡ ከስዊድን ዘላቂ ልማት ማህበር ጋር በጋራ ከሚሰሯቸው የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በተጨማሪ በቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትና አካባቢዎችን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ እንደሚገኙበት አመልክተዋል። የግብርና ምርታማነትን ማሳደግና ድርቅን ለመከላከል የሚያግዙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት የስምምነቱ አካል መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡ ከእጽዋት ተረፈ ምርትና ከብስባሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት የአፈርን ለምነትን የማጎልበት ሥራ ከማህበሩ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ዶክተር አትንኩት አመልክተዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም