የእስራኤል የልብ ህክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ህክምና ሊሰጡ ነው

232
ኅዳር  9 /2012 መቀመጫውን እስራኤል ያደረገው 'ሴቭ ኤ ቻይልድ'ስ ኸርት የተባለና ለትርፍ ያልተቋቋመው አለም አቀፍ የልብ ህክምና ቡድን ነገ በኢትዮጵያ የልብ ህከምና ማዕከል አገልግሎቱን ይሰጣል። ቡድኑ ለ30 ህፃናት የልብ ቀዶ ህክምና እና ሌሎች ተያያዥ ህክምናዎችን እንደሚሰጥ ፒአር ኒውስ ከዋሽንግተን ዘግቧል። 'የህፃናትን ልብ ማዳን' የሚል ተልዕኮ ያነገበው ቡድን በኢትዮጵያ የልብ ማዕከል ከሚሰሩትና የቡድኑ አጋር ከሆኑት ዶክተር ያየህይራድ መኮንን ጋር በመሆን በማዕከሉ ህክምናውን ይሰጣል ተብሏል። የቡድኑ አባላት በቆይታቸው ለህፃናት ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ሲሆን ከዚህ በፊት ህክምና ያገኙ ክትትል ይደረግላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረበትን 25 አመት ባለፉት ዓመታት በቡድኑ ህክምና ያገኙ 700 ኢትዮጵያውያን ህፃናት በተገኙበት ይከበራል። ቡድኑ በመላው አለም ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖትና ዜግነት ሳይለይ የህፃናትን ልብ ለማከም ይሰራል” ሲሉ የተቋሙ ዋና ተጠሪ ሲሞን ፊሸር ተናግረዋል። "በኢትዮጵያ የምናከናውነው ተልዕኮ ዘመኑ የሚጠይቃቸውን የልብ ህክምና ቁሳቁስ ከማሟላት አንስቶ፣ ላቦራቶሪ፣ ዘመናዊ የቀዶ ጥገና ክፍል እና የጽኑ ህክምና ክትትል ለማድረግ የሚያግዙ ባለሙያዎችንና ቁሳቁሶችን ማቅረብን ይጨምራል'' ብለዋል። በዚህም አገልግሎቱን የሚፈልጉ ህፃናትን ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው፤ ''በኢትዮጵያ የምናከናውነው ተልዕኮ የብዙ ልጆችን ህይወት የለወጠ ሲሆን በቡድናችንና በአጋሮቻችን ተግባር በእጅጉ እንደሰታለን” ብለዋል። 'ሴቭ ኤ ቻይልድ'ስ ኸርት' በኢትዮጵያ ዘጠኝ የልብ ህክምና ስፔሻሊስቶችን  አሰልጥኗል። ዘጠኙም ባለሙያዎቹ አሁን ላይ በአገራቸው ህክምናውን እየሰጡ እንደሚገኙም ተገልጿል። ተቋሙ ከተቋቋመበት አ.አ.አ 1995 አንስቶ በ62 አገሮች ለሚገኙ 5 ሺ ህፃናት የልብ ህክምና ሰጥቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም