የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚጠበቁበትን ተግባራት እያከናወነ አይደለም

113
ህዳር 8/2012 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አገሪቷ ከገባችበት ችግር ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚጠበቅበትን ተግባራት እያከናወነ አለመሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። ኮሚሽኑ በበኩሉ በህጉ የተሰጡትን ተግባራት ለመወጣት እንዲያስችሉት የሪፎርም ስራ ላይ መሆኑን ገልጿል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ የ2012 በጀት ዓመት እቅዱን አቅርቧል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዶንኤል በቀለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኮሚሽኑ አሁን የሚጠቀምበት የማቋቋሚያ አዋጅ 15 ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ "ተልእኮውን በአግባቡ ለመወጣት እያዳገተው ነው"። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ ለማዋቀር በሰው ኃይል፣ በገንዘብ አቅምና በሌሎች አስፈላጊ ጉዳዩች ላይ የሪፎርም ስራዎችን በማካሔድ ላይ ነው ብለዋል። አሁን ላይ ኮሚሽኑ ባለው አቅም በተለያዩ ቦታዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሪፖርት ለማድረግና ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ የሚያስችለው ቁመና ላይ አለመሆኑን ግን አልሸሸጉም። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የሰብአዊ መብት ቀውስና የኮሚሽኑ አቅም ላይ  በርካታ ጥያቄዎችን እያስነሳ ቢሆንም ኮሚሽኑ ይሕንን ለመሸከም የሚያስችለው ቁመና ላይ አለመሆኑንም አንስተዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኮሚሽኑ የሕዝቡን ብሶት ፣ሰብዓዊ መብት ረገጣና ሌሎች ችግሮች ለሚመለከተው አካል ከማቅረብ ይልቅ የዘገዩ እቅዶችን ለምክር ቤቱ ማቅረቡ አግባብነት የለውም ነው ያሉት። ሕዝቡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱበትን ችግሮችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት የሚያይለት አካል የሚፈልግ በመሆኑም ኮሚሽኑ ከዚህ አንጻር ራሱን ሊፈትሽ ይገባል ብለዋል። ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ አምስተኛ ወር ላይ ሆኖ ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው እቅድ የተሟላና በሚፈለገው መልኩ ቁልፍ ተግባሮቹን የለየ አለመሆኑ ነው የተገለፀው። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ፈይሳ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው በኮሚሽኑ ላይ ያነሱት  ሃሳብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በግልጽነት እንዲወጣ ለማድረግ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ በሪፎርም ስራው ላይ በመሆኑና ተቋም እየገነባ ያለና በዚህ ተግባር ውስጥ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፉን የሚያደርግለት ቢሆንም ኮሚሽኑ በእቅዱ ውስጥ የሁኔታዎችን ግምገማ በአግባቡ አለማስቀመጡን ነው የገለጹት። በሀገሪቷ የሰብአዊ መብትን ከማስከበር አንፃር በርካታ ችግሮች እንዳሉ አውቆም ኮሚሽኑ በምክር ቤቱ የተሰጡትን አስተያየቶች ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባውም ጠቁመዋል። በመሆኑም ኮሚሽኑ እነዚህን ክፍተቶችን በማስተካከል ሊራመድና ከሕብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም