የኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የቢዝነስ ፎረም እየተካሄደ ነው

65
ህዳር 8/2012 የኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የደቡብ ኮርያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የተገለጸው። በፎረሙ መክፈቻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ከደቡብ ኮርያ ጋር ያላትን ግንኙነት በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንቨስትመንትና ንግድ  ማጠናከር ትፈልጋለች። በኢትዮጵያ ውስጥና በውጪ አገር ሰፊ የገበያ አማራጭ መኖሩን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴታው፤ አገሪቷ አምራች የሰው ሃይል የሚገኝባትና ለኢንቨስትመንት የሚሰጡት ማበረታቻዎች አትራፊ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል። ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ የኤሌትሪክ ሃይል፣ ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን፣ የግብርና ማቀነባበሪያ መንግስት ቅድሚያ የሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እያካሄደችው ባለው የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ሊምሁን ሚም በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገሮች በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸው ግንኙነት ጠንካራ አለመሆኑን አመልክተዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በታች መሆኑንም ገልጸዋል። የደቡብ ኮርያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት መጠን 38 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ለአብነት ጠቅሰዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮርያ በሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ያህል በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍም ለማጠናከር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል። የበሶላር ኢነርጂ ላይ የተሰማሩት የደቡብ ኮርያ ባለሃብት ሚስተር ፓሲዮንግ ሆንግ በኢትዮጵያ የሚገኙ አማራጮችን በማየት በኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦተ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። በቢዝነስ ፎረሙ እየተሳተፉ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በበኩላቸው፤ በፎረሙ መሳተፋቸው ልምዶችን ለመለዋወጥና ትስስር ለመፍጠር እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል። በፎረሙ በግብር ማቀነባባሪያ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በግንባታና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ 36 የደቡብ ኮርያ ባለሀብቶች ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር እየተሳተፉ ነው። የኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የቢዝነስ ፎረም ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ የደቡብ ኮርያ ባለሃብቶች ከተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ቡና፣ የቅባት እህሎችንና የቆዳ ውጤቶችን ወደ ደቡብ ኮርያ በመላክ መድሃኒት፣ ተሽከርካሪና የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን ደግሞ ታስገባለች። ባለፉት 10 ዓመታት የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም