ሐብሊ ለሀገራዊ አንድነትንና ሰላም መጎልበት የድርሻውን እንደሚወጣ ገለጸ

65
ሐረር ኢዜአ ህዳር 8/2012፡- ሀገራዊ አንድነትንና ሰላምን የሚያጎለብቱ ተግባራት በመደገፍ የድርሻውን እንደሚወጣ የሐረሪ ብሐራዊ ሊግ /ሐብሊ/ ገለጸ። የሊጉ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ ተጀመረ። ጉባኤው ሲጀመር የሊጉ ሊቀመንበር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት ሐብሊ ሀገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ይተጋል፤ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንም ይሰራል። በተለይም በወሳኝ ሀገራዊ፣ ክልላዊና ድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ የአመለካከትና የተግባር አንድነት ለመፍጠር ሊጉ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ "በተለይ ጥንካሬዎችን አጎልብቶና ተግዳሮቶችን አቃሎ ሕዝቡንና ድርጅቱን የሚያሻግር አመራር መፍጠር ያስፈልጋል "ብለዋል፡፡ በመድረኩ ጥንካሬዎችን፣መልካም አጋጣሚዎችንና ክፍተቶችን መለየትና ለቀጣይ ተልዕኮ ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ  አመልክተዋል፡፡ "ወቅቱ ህልውናችንን የምናስጠብቅበት ነው "ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ጉባኤው በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማዳበር፣ ለቀጣይ ሥራ ራስን ለመዘጋጀትና ብቃት ያለው አመራር ለማውጣት የሚሰራበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በለውጡ ምንነት፣አስፈላጊነትና ባህሪያት ላይ ግንዛቤን በማዳበር ባስገኛቸው ውጤቶች፣ባጋጠሙ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ተወያይቶ  የጋራ አቋም መያዝ እንደሚገባም  አቶ ኦርዲን አመልክተዋል፡፡ ጉባኤው በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች መካከል የተፈጸመው ውህደት ላይ አተኩሮ እንደሚወያይም ይጠበቃል፡፡ በሊጉ በአስረኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና አፈጻጸጸማቸው መገምገም ሌላው የጉባዔው አጀንዳ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ''ሰላምና አንድነት ለሕዝባችን ህልውናችን!'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ጉባኤው ለአራት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም