የፈተና ዝግጅትና አስተዳደርን የሚያዘምን ባንክ ተዘጋጀ

99
    አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2010 የብሔራዊ ፈተና ዝግጅትና አስተዳደርን የሚያዘምን የፈተና ባንክ መዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ባለፉት ሶስት ዓመታት ዝግጅት የተደረገበት ሳይንሳዊ የሆነ የፈተና ባንክ ወይም ቋት ስራ ተጠናቋል። በመሆኑም ዘንድሮ የሚሰጡት ብሔራዊ ፈተናዎች ከስርዓተ ትምህርቱ ጋር የተያያዙ፣ የተጠኑ፣ የተመዘኑ፣ የተሞከሩና በትክክል በየትምህርት አይነቱ ዕውቀትና ክሕሎት የሚለኩ እንደሚሆኑ ነው የገለጹት። ከዚህ በፊት ፈተና 'ኤ' ፈተና 'ቢ' ተብሎ ይዘጋጅ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሳይንሳዊ መንገድ ከተዘጋጀው የፈተና ቋት በቀጥታ ተወስዶ ለተማሪው እንደሚሰጥ ነው የገለጹት። በፈተና አዘገጃጀት ብቻ ሳይሆን በስርጭትም ላይ ተሰርቷል ያሉት ዶክተር ጥላዬ፤ ባለፉት ዓመታት የነበሩትን ችግሮች በማጥናት በተቀናጀ መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላው አገሪቱ የሚደርስበትን አሰራር አጠናቀናል ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት በሚኒስቴሩ በኩል ፈተናዎችን ማጓጓዝ፣ ፈታኞችንና ሱፐርቫይዘሮችን የመመልመል ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አመልክተው ሕብረተሰቡም አደገኛ የሆነውን የመኮራረጅ ልምድ እንዲዋጋ ጥሪ አቅርበዋል። የፈተና ስራ ውስብስብና አስቸጋሪ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙትን ችግሮች በቅርበት በመገምገም ዘንድሮ እንዳይደገም ጥንቃቄ መደረጉን ነው ያብራሩት። ባለፉት ዓመታት ፈተና የማጉደልና የማዘበራረቅ ስራ የሰሩ ሰራተኞች በፈተናዎች ኤጀንሲ አማካኝነት የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን ዘንድሮ ይህ እንዳይከሰት በተሻለ ጥንቃቄና ተጠያቂነት እየተሰራ እንደሆነ ነው የገለጹት። በዘንድሮው የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ፣ የመሰናዶ ደግሞ ከ284 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተና ለመውሰድ ተመዝግበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም