ሴቶች ያለሙትን ግብ ለማሳካት ቅድሚያ የመንፈስ ጥንካሬን ማጎልበት አለባቸው - የበጎ አድራጎት ስራ ባለቤት የሆኑ ሴቶች

72
ኢዜአ፤ ህዳር 8/2012 ሴቶች ያለሙትን ግብ ለማሳካት ቅድሚያ የመንፈስ ጥንካሬን ማጎልበት እንደሚገባቸው የበጎ አድራጎት ስራ ባለቤት የሆኑ ሴቶች ተናገሩ። ዓለማችን ላይ በተሰማሩበት የስራ መስክ ጉልህ ስራ ሰርተው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ፣ ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረጉና ሃያልነታቸውንም ያስመሰከሩ ሴቶች በርካቶች ናቸው። ሴቶች በተለይም በሃላፊነት ቦታዎች ላይ ተቀምጠው በሚሰሯቸው ስራዎች ውጤታማ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘም የውሳኔ ሰጪነት ብቃታቸውና ቁርጠኝነታቸው አብሮ ተያይዞ የሚነሳ ነው። በአገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን የቻሉ ስኬታማ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በርካቶች ናቸው። ሴቶች የማይሳተፉባቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በግማሽ እውቀት፣ በግማሽ ጉልበትና ጥረት ላይ የተመሰረተ መሆኑም ይነገራል። ሴቶች የማህበረሰቡ የጀርባ አጥንት ከመሆናቸውም ባሻገር ለቤተሰባዊና አገራዊ እድገትም አስተማማኝ መሰረቶች ስለመሆናቸውም ብዙዎች ይስማሙበታል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የእርሻ ሥራ በሚተዳደሩ የአርሶ አደር ቤተሰቦች ውስጥ በገጠራማ አካባቢ ይኖራሉ። በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ደግሞ ሰፊ የሰው ጉልበት በሚጠይቀውና ሕጻናትን ጨምሮ ሁሉም ሰው አድካሚ የጉልበት ሥራ ከሚሠራበት የገጠሩ የግብርና ኢኮኖሚ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውም ይታወቃል። ታዲያ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶች ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስና አላማቸውንም ለማሳካት ቅድሚያ የ"እችላለው" እና የመንፈስ ጥንካሬን ማጎልበት እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የበጎ አድራጎት ስራ ባለቤት የሆኑ ሴቶች ይገልጻሉ። የኒያ ፋውንዴሽን (የጆይ አውቲስቲክ ልጆች ማዕከል) መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዘሚ የኑስ እንደሚሉት፤ "ሴቶች በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የመስራት አቅም አላቸው"። የቤት ውስጥ ሥራ ከማከናወንና ልጆችን ከመንከባከብ ባሻገርም "በከፍተኛ የስራ ቦታ ላይም ሃላፊነትን በአግባቡ የመወጣት ብቃት አላቸው" ብለዋል። ይሁንና እነዚህን ሃላፊነቶች ለመሸከምና አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታዎችን ለማለፍ በቅድሚያ "የመንፈስ ጥንካሬን ማበልጸግ ይጠበቅባቸዋል" ሲሉም ተናግረዋል። ሃሳብና ፍላጎትን በተገቢው መንገድ በመገምገምና በሚቻለው አቅም በመጠቀም መትጋት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች ወይዘሮ መሰረት አዛገ በበኩላቸው፤ "ሴቶች ተፈጥሮአዊ ጥንካሬን የተላበሱ ናቸው"። በተለይም በቤታቸው፣ በአካባቢያቸው፣ በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ ሚና ማበርከት የሚያስችል "እምቅ አቅም አላቸው"። ይህን ውስጣቸው ያለውን አቅም በመጠቀምም ለራሳቸው ብሎም ለአገራቸው ልማትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉም ይናገራሉ። በመሆኑም ያላቸውን አቅም በመጠቀምና ሚናቸውን በማጎልበት የጠንካራ መንፈስ ባለቤት መሆናቸውንም ማስመስከር አለባቸውም ብለዋል። በኢትዮጵያ ከ100 ሚሊየን በላይ ህዝብ እንዳለ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ መካከልም 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም