የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ማህበራት መጠናከር አለባቸው - ኢንጂነር ታከለ ኡማ

117
ኢዜአ፤ ህዳር 8/2012 የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች መመለስ እንዲቻል በተለይ ማህበራት መጠናከር እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አሳሰቡ። የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር "የተደራጀ የሴቶች ተሳትፎ ለተሻለ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል። በጉባኤው ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደገለጹት፤ በሴቶች የሚነሱ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ እንዲቻልም በጠንካራ አደረጃጀት የተቋቋሙ ማህበራት መንግስትና ህዝብ ይፈልጋሉ ብለዋል። በዚህም በተለይ የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች መመለስ እንዲቻልና ተሳትፏቸውንም ለማጎልበት ማህበራት መጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል። ሴቶችን ለመደገፍ ብሎም ከተማዋ ለእናቶችና ህጻናት ምቹ እንዲትሆንና ጥያቄዎቻቸውን መመለስ እንዲቻል በማድረግ ረገድ ከተማ አስተዳደሩ እገዛውን እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። የማህበሩ ፕሬዚደንት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ታዘዝ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ባለፉት ጊዜያት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ሴቶች ከጓዳ ወደ አደባባይ እንዲወጡ፣ አቅማቸው እንዲጎለብትና በበጎ ፍቃድ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ብሎም የመብት ተሟጋች ሴቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ረገድም ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ባሻገርም ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችንም ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙና የሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩም ጠንካራ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም በተለይ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንደነዚህ ያሉ ማህበራትን በመደገፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲችሉም ጥሪ አቅርበዋል። የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋይ፤ በአገሪቷ ባለፉት ጊዜያት የሴቶችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሲሰሩ እንደቆዩ ጠቁመዋል። በከተማና በገጠር የሚኖሩ ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራትና ድርጅቶች ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል። ከእነዚህም በተገኙ ለውጦች የሴቶች ማህበራት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበርም አውስተዋል ሚኒስትሯ። መንግስትም የሴቶችን አደረጃጀቶች የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል። በጉባኤው ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የበጎ አድራጎት ማህበራትና በርካታ የማህበሩ አባላት ተሳትፈዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ከተቋቋመ 21 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ40 ሺህ በላይ አባላት አሉት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም