ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ሊጠቀሙባቸው ይገባል

221
ኢዜአ፤ ህዳር 8/2012 ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ ተጠቆመ። የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ‘’ማህበራዊ ሚዲያን ለልማት’’ በሚል መሪ ሀሳብ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ዛሬ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል። በኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚዲያ/ፌስ ቡክ/ ላይ ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው ታዋቂ ሰዎች በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት ወጣቱ ማህበራዊ ሚዲያን ሲጠቀም በአስተውሎትና በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ  ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ከአገሪቷ አጠቃላይ ህዝብ ቁጥር 5 በመቶውን ብቻ ይይዛል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ከ15 እስከ 30 እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ታዲያ በፌስ ቡክ አካውንቶች የሚለቀቁ መረጃዎች የአገርን ደህንነት የማይጎዱ፤ ወጣቶችን ለአላስፈላጊ ሁከት የማይዳርጉና ትክክለኛና ግልጽ ሊሆኑ ይገባል። አሁን አሁን በአገሪቷ እየታየ ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ይሁንና በፌስ ቡክ የሚለቀቁ መረጃዎች ሙሉ በሙሉ የጥፋት መረጃዎች ናቸው ብሎ መደምደም ግን አይቻል። ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት እንደሚለው በርካታ ወጣት በፌስ ቡክ የሚለቀቁ መረጃዎች በሙሉ ትክክለኛና አስተማሪ ነው ብሎ ያስባል። ነገር ግን አንዳንድ የመረጃ ሚዛናዊነትን ያልጠበቁ፣ የተሳሳቱና ለጊዜያዊ ጥቅም አገራቸውንና ህዝባቸውን ለአላስፈላጊ ሁከትና ብጠብጥ የሚዳርጉ እንዳሉ ጠቁሟል። ወጣቱም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት መረጃዎችን ሃሳባቸውን በመመርመርና ትክክለኝነታቸውን በማረጋገጥ ብቻ መጠቀም ይገባቸዋል ይላል። ብዙ ጊዜ ወጣቶች ከስሜታዊነት በመነጨ በፌስ ቡክ ከሚተላለፉ መረጃዎች የሚፈልገውን መርጦ የማንበብ አዝማሚያ ይስተዋላል። "ቁንጽል ሃሳቦችን ይዞ ለሌላ የማጋራት ሁኔታም እንዳለ" ጋዜጠኛ ኤልያስ ተናግሯል ። ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በበኩሉ "በፌስ ቡክ የሚለቀቁ መረጃዎችን መዝኖ ያለመጠቀም አብሮ የመኖር እሴታችንን ጎድቶታል"። ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት የሚያስተላላፉ ሚዲያዎች በብዛት ያለመኖር ደግሞ ወጣቱ ያገኘውን መረጃ ሁሉ እውነት አድርጎ የመውሰድ ዝንባሌ እንድያሳይ አድርጎታል ይላል። ይህንን ችግር ለመፍታትም በአገሪቷ ያለው የመተሳሳብ፣ አብሮ የመኖርና ፍቅር እንዲጸና ከቤተሰብ ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት ወጣቱን ማነጽና ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል። በአገሪቷም የጥላቻ ንግግርና የተሳሳተ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦች በህግ የሚጠየቁበት አግባብ ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል። የሄሎ ዶክተር መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ራሄል ሞገስ በበኩለቸው "ወጣቱ የፌስ ቡክ አጠቃቀም እውቀት ማነስ ለማህበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት ይዳርገዋል" ብለዋል። አብዛኛው በሄሎ ዶክተር የስልክ መስመር የሚጠየቁ ጥያቄዎች ከጭንቀትና እንቅልፍ ከማጣት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ  የስነ ልቡና ችግሮች መሆናቸውንም ገልጸዋል። ይህ ደግሞ በብዛት ማህበራ ሚዲያን መጠቀምና ለሌላው የዕለት ተዕለት ስራቸው ብዙ ትኩረት መስጠት ያለመቻል ችግር እንደሆነ ይስተዋላል ብለዋል። የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ ጊዜውን በተወሰኑ ነገሮች ላይ ብቻ የማጥፋቱ ተግባርም ትውልድ የመቅረጽ ተግባርን ይጎዳል ነው ያሉት። ስለዚህ ማህበሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለወጣቱ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀመን ለማሻሻል መስራት አለበት ብለዋል። ወጣቶች በበኩላቸው በመንግስት ሚዲያዎችና ታማኝ ምንጮች ተገቢውን መረጃ በተገቢው ሰዓት ስለማያገኙ ለአላስፈላጊ የመረጃ መዛባት እንደሚዳረጉ ይናገራሉ። ስለዚህ መንግስት ትክክለኛ መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎችንና ግለሰቦችን በማበረታታት ሌሎችን ደግሞ ተጠያቂ የማድረግ ስራ መስራት አለበት ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም