የጸረ ተህዋስያን መድሃኒቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ከህዳር 8 -12 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል

73
ኢዜአ ህዳር 08 / 2012 ዓ.ም የጸረ ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግር ምክንያት በዓለም ላይ ከ700 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በየዓመቱ እንደሚሞቱ ጥናቶች አመላከቱ። ቀላልና ከባድ በሽታዎች ህመሙ ሳይባባስ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድና በህክምና ባለሙያ በተደገፈ የጸረ ተህዋስያን መድሃኒት በመውሰድ ወደ ቀድሞ ጤና መመለስ ይቻላል። ይሁን እንጂ እነዚህን እንክብሎች በተደጋጋሚ መውሰድ ወይም በአግባቡ አለመውሰድ መድኃኒቶቹ በጀርሞቹ መላመድን ስለሚያስከትል  በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከመድሃኒትነት በዘለለ እያመጣ ያለው የጎንዮሽ ጉዳት የባሰ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። ሚኒስቴሩ ይሂንን ችግር ተረድቶ ለመከላከል የሚያስችል ከህዳር 8 -12 ለአምስት ቀናት የሚቆይ የጸረ ተህዋስያን መድሃኒቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ያዘጋጀ ሲሆን ይህንን አስመልክቶም ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በግንዛቤ ማስጨበጫው መርሃ ግብሩ ማብሰሪያ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት የግንዛቤ መስጨበጫ መርሃ ግብር የተለያዩ ትምህርቶችን በመስጠት ይከበራል። በተለይም ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድሃኒቶች በኮንትሮባንድ ወደ ሃገር መግባታቸውና ምንም አይነት የጤና ባለሙያ ሳያማክሩ መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች መብዛታቸው ደግሞ ታማሚዎቹ ሰውነታቸው መድሃኒቱን እንዲላመድና በቀላል ህክምና መዳን እየቻሉ ህይወታቸውን ለማጣት እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዶክተር ሊያ አያይዘውም ሚኒስቴሩ የችግሩን ስፋት በመገንዘቡም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት የጋራ መድረክ ማመቻቸቱን ገልጸዋል። የምግብ መድሃኒትና ጤና አጠባበቅና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው በተለያዩ አካባቢዎች በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡ መድሃኒቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይኸንን ችግር ለመፍታትም ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ይላሉ። ህገ ወጥ መድሃኒቶች ወደ ሃገር እንዳይገቡ በመከላከልና የሚፈለጉ መድሃኒቶችን ወደ አገር ወስጥ በማስገባት ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት እንዲሰጡ እየተሰራ ነውም ብለዋል ወይዘሪት ሄራን። የትኛውም ዜጋ የህክምና ባለሙያን ሳያማክር ምንም አይነት መድሃኒት መውሰድ እንደሌለበትና በባለሙያ የታዘዘን መድሃኒት ደግሞ ሳይጨርሱ ማቆም መድሃኒቱ እንዲላመድ በማድረግ ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳርግ የገለጹት ደግሞ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ናቸው። የጸረ ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግር ምክንያት በዓለም ላይ ከ700 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በየዓመቱ እንደሚሞቱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ የገለጹት ዳይረክተሩ፤ በዚህ ከቀጠለ የችግሩ ስፋት እየተባባሰ እንደሚመጣም ገልጸዋል። የፀረ ተህዋስያን መከላከል ሳምንቱ በዓለም ለአምስተኛ ጊዜ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን የዘንድሮው ''የጸረ ተህዋስያን መድሃኒቶች እጣ ፋንታ ሁላችን እጅ ላይ ነው'' የሚል መሪ ሐሳብ አንግቧል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም