በትግራይ ከ17 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ውድድር ዛሬ በአድዋ ከተማ ተጀመረ

62
መቐለ ኢዜአ ህዳር 08/12 ዓ/ም--በትግራይ ክልል ከ17 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ታዳጊ ስፖርተኞችን የሚሳተፉበት ዓመታዊ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር ዛሬ በአድዋ ከተማ ተጀመረ። የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴረሽን ፅህፈትቤት ስራ አስፈፃሚ አቶ ገብረጊዮርግስ ጎይተኦም በውድድሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ውድድሩ ሁለቱም ጾታዎች የሚካሔድ ነው ። የውድድሩ ዋና ዓላማ ከክልሉ ብዛት ያላቸው ተተኪ አትሌቶች ለማፍራት ነው ብለዋል። በውድድሩ የሚያሸንፉ ታዳጊ አትሌቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ዓመታዊ የአትሌቲክስ ውድድር ክልሉን ወክለው እንዲሳተፉ ይደረጋል ። በዓድዋ ከተማ ስታድዮም ዛሬ በተጀመረውና ከክልሉ 11 ወረዳዎችና 8 ፕሮጀክቶች የተመለመሉ ከ150 በላይ ታዳጊ ስፖርተኞች ተሳታፊ መሆናቸው ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል። ውድድሩ ከ100 ሜትር ጀምሮ እስ 1ሺህ 500 ሜትር ባሉት የአጭርና መካከለኛ ርቀቶች ያካተተ ነው ተብሏል። በውድድሩ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ የዘርፉ አሰልጣኞች መካከል የትግራይ ደቡባዊ ዞን የኦፍላ ወረዳ አትሌቲክስ አሰልጣኝ ተፈሪ ግደይ በሰጡት አስተያየት ወረዳውን ወክለው የሚወዳደሩ 30 ወጣት ሴትና ወንድ አትሌቶች ማሳተፋቸውን ገልፀዋል። ክልልና አገር ወክለው መወዳደርና ጥሩ ውጤት ማምጣት የሚችሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት  በታዳጊ  ወጣቶች ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ያሉት አሰልጣኝ ተፈሪ ዛሬ የተጀመረው የክልሉ ዓመታዊ ውድድርም የዚህ አንድ አካል መሆኑን ተናግረዋል። የአትሌቲክስ ውድድሩ ሲጠናቀቅ ለኮኮብ ተጫዋቾችና ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ ወረዳዎች የገንዘብ ፤ የሜዳልያና የስፖርት ትጥቅ ማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ከውድድሩ መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም