በከተሞች የእድገት ፕላን የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያገዝ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመሀንዲሶች ተሰጠ

64
ኢዜአ ህዳር 07/2012   በትግራይና አፋር ከተሞች የሚስተዋሉ የዕድገት ፕላን እና ቅየሳ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከሁለቱ ክልሎች ለተወጣጡ መሀንዲሶች ተሰጠ። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ለአስር ቀናት ሲሰጥ በቆየው ስልጠና 161 መሀንዲሶች ተሳትፈዋል። ስልጠናው ትናንት ሲጠናቀቅ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉአለም ገብረጊዮርጊስ እንደገለጹት በሁለቱ ክልሎች በተለይ በማደግ ላይ ባሉ መካከለኛና አነስተኛ ከተሞች  የዕድገት ፕላን አለማዘጋጀት፤ ቅየሳ አለማካሄድ እና ወሰን የማስከበር ክፍተቶች ይስተዋላል። ይህም ህብረተሰቡ እንደ መልካም አስተዳደር ችግሮች   የሚነሳቸው ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እንዲያግዝ ለመሀንዲሶች የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚያግዝ ዶክተር ሙሉአለም ተናግረዋል። ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከአፋር ክልል የመጣው መሃንዲስከድር ዓሊ በክልሉ እያደጉ ከመጡ ከተሞች ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የወስን መጋፋትና አለመግባባቶች ችግር ለመፍታት ስልጠናው ተጨማሪ አቅም ሆኖ እንደሚረዳው ተናግረዋል። ስልጠናው በምህንድስና ቴክኖሎጂ ታግዞ በተግባር የተደገፈ መሆኑን ጠቁሞ  ይህን በመጠቀም የህብረተሰቡ ችግር ለማቃለል እንደሚጥርም ገልጿል።ከትግራይ ከልል በስልጠናው የተሳተፈው መሃንዲስ አሉላ ፍስሃ በበኩሉ በስልጠናው  ያገኘውን  ዕውቀት ተግባር ላይ በማዋል የህብረተሰቡ ችግሮች ለማቃለል የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል። በፕላን ዝግጅት ላይ የሚታዩ አስተዳደራዊና ቴክኒካዊ ክፍተቶች በዘላቂነት ለመፍታት በሙያው ጠንክሮ እንደሚሰራም አመልክቷል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም