የሦስቱ አገሮች የውሃ ሚኒስትሮች ድርድር አድርገዋል

70
ኢዜአ ህዳር 7/2012 የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮችና የቴክኒክ ቡድን አባላት ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር አጠናቀዋል። የሦስቱ አገሮች መሪዎች እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር መስከረም 2015 በሱዳን ካርቱም የተፈረመውን ስምምነት እና ከዚህ በፊት የነበሩ የቴክኒክ ውይይቶችን መሰረት በማድረግ ድርድሩን አካሂደዋል። ሚኒስትሮቹ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ነው ድርድር ያደረጉት። ድርድሩ ካርቱም ላይ ተለይተው በነበሩ ስድስት ነጥቦች ላይ ትኩረት በማድረግ የተካሄደ ሲሆን የሦስቱም አገሮች ሚኒስትሮች በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት ውይይት አድርገውበታል። ሦስቱ አገሮች ለሁለት ቀናት ያደረጉትን ድርድር በተመለከተ የውሃ፣ መስኖና ኤሌትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በድርድሩ ስምምነት የተደረሰባቸው መስኮች በአረንጓዴ መዝገብ እንዲመዘገብ ሲደረግ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ደግሞ በቀይ መዝገብ እንዲመዘገብ ተደርጓል። የሦስትዮሹ ውይይቱ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት የውይይት መድረኮች በእጅጉ መሻሻል የታየበት እንደሆነም ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል። በቀጣይ ለሚካሄደው ድርድር ሦስቱ አገሮች የሚመሩበት ሰነድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በአዲስ አበባ በተደረገው ድርድር ላይ ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የግብጹ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር ሞሐመድ አብደልና የሱዳኑ አቻቸው ፕሮፌሰር ያሰር አባስ ፈርመዋል። ቀጣዩ ድርድር በግብጽ ካይሮ ህዳር 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። በአዲስ አበባ ህዳር 5 እና 6 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው የሦስቱ አገሮች ድርድር ላይ ከአሜሪካና ከዓለም ባንክ የመጡ ታዛቢዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም