አገሪቱ በኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ዘርፎች ማተኮር ይገባታል-ምሁራን

69
ኢዜአ ኅዳር 07 / 2012 አገሪቱ ትኩረቷን ከፖለቲካ አጀንዳ በማውጣት ወደ ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ ዘርፎች እንድታዞር የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። የዩኒቨርሲቲው አንዳንድ ምሁራን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳመለከቱት አገሪቱ ወደ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ ልማቷ መመለስ አለባት። በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ዶክተር ጌታቸው አየለ እንደገለዑት አገሪቱ ለዘመናት በተከማቹ ፖለቲካዊ ችግሮች በሌሎች መስኮች እንዳታተኩር መቆየቷንና ጽንፈኞች ደግሞ በተለይ ወጣቱን የግጭት አጀንዳ አስታጥቀው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ማሰማራታቸው ያስታውሳሉ ፡፡ ሆኖም ምርትና ምርታማነትን እንደዚሁም የምንዛሪ እጥረት ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር ለውጥ እንዲመጣ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ፖለቲካው ለፖለቲከኞችና ለዘርፉ ባለሙያዎች መተዉ እንዳለበት የሚናገሩት ዶክተር ጌታቸው፣ በሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ አካላት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በተለይ የማህበራዊ ዘርፍ ምሁራን የወጣቱን አመለካከት የሚገሩ ፣ በሕዝቦች መካከል ያሉ ትሥሥሮችንም የሚያጠናክሩ በጥናት የተደገፉ ምክረ-ሀሳቦችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም መክረዋል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ከፖለቲካ አጀንዳዎች ይልቅ ለሕይወት ጠቃሚ መረጃ ልንዋወጥበት ይገባል ሲሉም ሐሳባቸውን ሰጥተዋል ፡፡ በዚሁ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ዶክተር ብርሃኑ ጌትነት በበኩላቸው በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለው አክራሪነትና መገፋፋት የሰላም መደፍረስ እያስከተለ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራበትን ሁኔታ በመውጣት የኢንቨስትመንት ደህንነት በማረጋገጥ የኢንቨስትመንትና ንግድ እንቅስቃሴውን ማሳደግ ይገባል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ ዶክተር ብርሃኑ ገለፃ የሰላም እጦት በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ የሚገኙት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ቢሆንም፤ ፈጣንና አስከፊ ጉዳት የሚያደርሰው ሰፊውና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለው የኅብረተሰብ  ክፍል ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦችን በማፍለቅ አፍራሽ አመለካከቶችን ማሸነፍ እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም