ምክንያታዊ በመሆን ነገሮችን መመርመር አለመቻላችን የቁማርተኞች መጫወቻ አድርጎናል --- ምሁራን

49
አዲስ አበባ ህዳር 6 / 2012  ”ምክንያታዊ በመሆን ነገሮችን መመርመር አለመቻላችን የፖለቲካ ቁማርተኞች መጫወቻ አድርጎናል” ሲሉ ምሁራን ገለጹ። ግጭቶችን ለመከላከልና ለመፍታት የሃሳብ ልዩነቶች ላይ ውይይት ማድረግና ሁሉም ሰው ስለሰላም ያገባኛል የሚል አመለካከት መያዝ እንዳለበትም አመልክተዋል። በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሳሳቱ ወሬዎች ሲናፈሱ ምክንያታዊ በመሆን ማረጋገጥ እንዳለባቸውና የስልጣን ጥም ያለባቸው ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ አስገንዝበዋል። ምሁራኑ በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የአገሪቱ የትምህርት ጥራት እየወደቀ መምጣቱ ትውልዱ ምክንያታዊና አመዛዛኝ እንዳይሆን ማድረጉ አሁን ላይ እየታዩ ላሉ ግጭቶች መነሻ ሆኗል። ዶክተር ገበያው ጥሩነህ ሀኪምና መምህርና ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የሚቀርጹ መምህራን ብቃት በሚፈለገው ልክ አለመሆንና ከዚህ መውጣት አለመቻሉ ተማሪዎች በግጭቶች እንዲሳተፉና ከአገርና ከቀጠና እንዲሁም አህጉር ይልቅ ጠበው ስለጎሳቸው ብቻ እንዲያስቡ ማድረጉንም ገልፀዋል። ከዚህ ቀደም ልዩነት የሚፈታው በውይይትና በመነጋገር እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይ በ1960ዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ስለህዝብ ጥያቄ ሃሳብ የሚንሸራሸርባቸው መድረኮች እንደነበሩ አውስተዋል። ሰዎች በሃሳባቸው መገደል ሲጀምሩ የመናገር መብቶች እየተገደቡ የውይይት ባህል መቀዝቀዙን አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) የሰው አስተሳሰብ በብሄር፣ ክልልና ጎሳ እንዲታጠር በማድረጉ የተዘራው ዘር እያፈራ መጥቶ አሁን ለሚታየው ግጭት መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲዎች ሀገርን የሚለውጡ የምርምርና አዳዲስ ሃሳቦች መፍለቂያ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የብጥብጥና ግጭት ማዕከል ሆነው እንዲታሰቡ ማድረጉን ገልፀዋል። እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ራስን አሳልፎ መሰጠትን የሚሻው የልብ ትምህርት ላይ አለማተኮራቸው እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መሆኑ አንዱ የሌላውን ቁስል እንዳይረዳና መተሳሰብ መቀነሱን አብራርተዋል። እሴቶቻችን መሸርሸራቸውና ምክንያተዊነትን ማጣታችንም ለፖለቲከኞች ቁማር መጫወቻ አድርጎናል ይላሉ። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት ተማሪዎች መወያየትን መልመድ እንዳለባቸውና መምህራንም የውይይት መድረኮችን ማመቻቸት እንዳለባቸው ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች በአንድ ላይ የሚሰባሰቡባቸው መሆኑ ለግጭት ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ገልጠዋል። በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ሳይሰፉ ለመቆጣጠር ተቋማቱ ከፀጥታ አካላትና ከኀብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንዲሰራም ጠይቀዋል። አገሪቱን ለመጉዳት አቅደው የሚሰሩ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውንና እነሱንም እየደገፉ ያሉ የውስጥ ኃይሎች መኖራቸውን ልብ በማለት የህዝቡን ጥያቄ በማወያየትና በመለየት መፍትሄ መስጠት እንዳለበትም እንደሚገባ አመልክተዋል። የፖለቲካ ቁማርተኞች በሚጭሩት ግጭት ተጎጂ ደሃው ኀብረተሰብ በመሆኑ ህዝቡ ዝምታውን ሰብሮ ያገባኛል ማለት እንዳለበትም አስረድተዋል። በግጭት የፈረሱ አገሮች የችግራቸው መፍቻ ያደረጉት ውይይት መሆኑን ጠቁመው አገር ሳይፈርስ በፊት ውይይትን ማስቀደም ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል። መንግስትም በመዋቅሩ ውስጥ ሆነው ግጭት የሚቀሰቅሱ ኃይሎችን መፈተሽ እንዳለበትና የህግ የበላይነትን ለማስከበርም ከህዝቡ ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበት ገልፀዋል። የተሳሳቱ አረዳዶችን ለማጥራትና የአንዱን ቁስል አንዱ እንዲረዳ ለማድረግም መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል። “ኀብረተሰቡ አገሪቱን እስካሁን አፅንቶ ያቆያትን የመተሳሰብና የመከባበር እንዲሁም ሌሎች እሴቶች ለወጣቶች ማስተማር መቻል አለበት” ብለዋል። ምሁራንም የውይይት ባህል እንዲያድግና የህዝብ ጥያቄዎች መፍትሄ እንዲያገኙ መድረክ መፍጠርና ሃሳብ በማፍለቅ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም