በምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ምክንያት በምንፈልገው መጠን ማምረት አልቻልንም---በትግራይ በቢራ ገብስ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች

81
ማይጨው (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2012ዓ.ም---ከቢራ ገብስ የተሻለ ተጠቃሚ ብንሆንም በምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ምክንያት በምንፈልገው መጠን ማምረት አልቻልንም ሲሉ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለጹ። የአላማጣ ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ ዘር የሚያባዙ ማህበራት ባለመኖራቸው የቢራ ገብስ ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ችግር መፈጠሩን አስታውቋል፡፡ በእምባ አለጀ ወረዳ የዓይባ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በዞኑ የቢራ ገብስ ከሚመረትባቸው ቀበሌ ገበሬ ማህበራት አንዱ ነው፡፡ በአይባ ቀበሌ የአርሶአደሮች  ሕብርት ሥራ ማህበር ኃላፊ አርሶ አደር ሀፍቱ ፀጋይ እንዳሉት "ጂ ኤም ኤስ" ከተባለ የቢራ ገብስ ገዢና አቅራቢ ድርጅት ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሮች ምርጥ ዘር እንደሚያከፋፍሉ ተናግረዋል። የቢራ ገብስ ምርት ሲደርስም በወቅቱ ካለው የቢራ ገብስ ዋጋ 20 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ከአርሶ አደሩ እንደሚገዙ አርሶ አደር ሀፍቱ ገልጸዋል፡፡ "በአይባ ቀበሌ ከ137 የሚበልጡ የቢራ ገብስ አምራች ፍቃደኛ አርሶ አደሮች ቢኖሩም ዘሩ በቀላሉ ስለማይገኝ ለሁሉም አርሶ አደር ማዳረስ አልተቻለም" ብለዋል። የአርሶ አደሮች የቢራ ገብስ ፍላጎት እያደገ ቢሆንም በምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ምክንያት ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንዳልተቻለ ኃላፊው አመልክተዋል። "ይህም አርሶ አደሩ ልማቱን አስፍቶ የበለጠ ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል" ብለዋል። ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ግርማይ ረዳኢ በበኩላቸው የሚያመርቱትን የቢራ ገብስ በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በክረምቱ የመኽር እርሻ በአንድ ጥማድ መሬት 14 ኩንታል የቢራ ገብስ አምርተው ለሕብረት ሥራ ማህበሩ በ22 ሺህ ብር መሸጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም በፊት ይዘሩት ከነበሩት የአካባቢው ገብስ ጋር ሲነጻጸር በምርትም በዋጋም የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ "ጥቅሙን በመረዳት በቢራ ገብስ የሚሸፈነውን መሬት ወደግማሽ ሄክታር ለማሳደግ ፍላጎት ቢኖረኝም በዘር አቅርቦት ምክንያት በአንድ ጥማድ መሬት ብቻ ተገድቢያለሁ" ብለዋል። የአላማጣ ግብርናና ምርምር ማዕከል የገብስ ማዳቀል ተመራማሪ አቶ ሙእዝ መሓሪ በበኩላቸው ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ "አብኒ፣ ኤኤች 1847 እና አይበን" የተባሉ የገብስ ዘሮችን በዞኑ የማዳቀል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡ አቶ ሙእዝ እንዳሉት የቢራ ገብስ ዝርያዎች በአንድ ሄክታር መሬት እስከ 30 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ እና በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተሻለ ነው። ዞኑ ለቢራ ገብስ ተስማሚ ምህዳር ያለው በመሆኑ አርሶ አደሮችን በስፋት በማሳተፍ በምርታማነትና በዋጋ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ "ይሁንና የቢራ ገብስ ዘር የማባዛት ሥራ የሚሰራ አካል ባለመኖሩ አርሶ አደሩ በሚፈለገው መጠን ዘሩን አግኝቶ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጓል" ብለዋል። "ማዕከሉ የማዳቀል ሥራ ስለሚሰራ ለሁሉም አርሶ አደር የሚበቃ ዘር ማቅረብ አልተቻለም" ብለዋል አቶ ሙእዝ። የትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት ኃላፊ ተወካይ አቶ አሰፋ አስረስ በበኩላቸው በዞኑ ለቢራ የሚሆን የገብስ ዘር እጥረት መኖሩን አምነው ችግሩን ለመቅረፍ ዘርን ከምርምር ማዕከላት በመውሰድ የማባዛት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል። የራያ ቢራ ፋብሪካ በየአመቱ 100 ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ በግብአትነት እንደሚጠቀም የገለጹት ደግሞ የገብስ ብቅል አቅራቢ የአለም አቀፍ ገበያ ስርአት(ጂ.ኤም.ኤስ) አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ሓለፎም ናቸው፡፡ አብዛኛው የፋብሪካው ግብአቶች ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎችና ከውጪ አገር እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡ ዞኑ የቢራ ገብስ ለማምረት ተስማሚ ምህዳር ያለው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቴዎድሮስ ፣ በአግባቡ ከተሰራበት ለራያ ቢራ ፋብረካ የሚሆን ገብስ ሙሉ ለሙሉ ከአካባቢው ለመሸፈን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ እንደአስተባባሪው ገለጻ የቢራ ገብስ አምራች አርሶ አደሮች ፍላጎት እያደገ ቢመጣም የዘር እጥረት በመኖሩ በሚፈለገው ደረጃ ማቅረብ አልተቻለም፡። "ፋብሪካው 100ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ በግብአትነት የሚጠቀም ቢሆንም ከዞኑ መሰብሰብ የተቻለው ምርት ከአንድ ሺህ ኩንታል አይበልጥ" ብለዋል፡፡ በዞኑ አስካሁን የቢራ ገብስ በማምረት ስራ የተሰማሩ የአርሶ አደሮች ቁጥር ከ386 እንደማይበልጡ ታውቋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም