በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ የታቀደው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ እስካሁን አልተጀመረም

3327

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ የታቀደው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ እስካሁን በገንዘብ እጥረት ምክንያት አለመጀመሩን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ10 ወራት እቅድ አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል።

በድሬዳዋ፣መቀሌ፣አዳማ፣ጅማና ኮምቦልቻ ከተሞች 36 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ታቅዶ ነበር።

ሚኒስቴሩ እንዳለው ፓርኮቹ በሚገነባባቸው በከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ከ300 ሺህ ብር በላይ መክፈል እንደሚችሉ በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የፖሊሲና ፕሮግራም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድዘይን ከድር እንዳሉት፤ግንባታውን ለማካሄድ ከፍተኛ በጀት በማስፈለጉ ግንባታውን መጀመር አልተቻለም።

ሚኒስቴሩ የመኖሪያ ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ ስትራቴጂዎችን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ኃላፊው በ2011 ዓ.ም በ20/80 ፕሮግራም 79 ሺህ ቤቶች፣ በ40/60 ደግሞ 21 ሺህ 240 ቤቶች ለማጠናቀቅ መታቀዱን አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በበጀት ምክንያት እንዳይስተጓጎል ምን የተቀመጠ አቅጣጫ አለ? በተለይ እንዱስትሪ ፓርኮች በሚገነባባቸው ከተሞች በምን መልኩ ለመደገፍ አስቧል? ሰነድ አልባ ይዞታዎችን ወደ ህጋዊነት ለመመለስ ምን ያህል መረጃ ላይ የተመሰረተ ሥራ ይከናወናል የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር አባይ በሰጡት ማብራሪያ የበጀት እጥረቱን ለመፍታት ሚኒስቴሩ በመሰረታዊነት ሁለት አማራጮችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው።

የመጀመሪያው ማህበራት በአቅርቦቱ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የግል ባለኃብቱ ከመንግስት ጋር በመሆን ቤቶችን ሰርቶ የሚያስረክብበት ሁኔታ እየታሰበ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከሰነድ አልባ ሥራዎች የተያያዙ ሥራዎች ቀድመው መጠናቀቅ ነበረባቸው ያሉት ሚኒስትሩ በቀጣዩ በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ በጥናት የተደገፈ ተግባራት ይከናወናሉ።

የሊዝ አዋጅ፣ የካሳ አዋጅና አገር አቀፉ የከተማ ፕላን ጸድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፉፊ ደልጌሳ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በጊዜ አለመጠናቀቅ ትልቅ ፈተና ሆኗል፤ በዚህም የዋጋ፣ጊዜ እና ጥራት ብክነት በመከሰቱ ህዝቡም እሮሮ እያሰማ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴሩ ችግሮችን በመለየትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ቤቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የመሬት ይዞታና ምዝገባ፣ የካዳስተር ሥራዓት ዝርጋታ አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት እንዲሰራ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።