የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን 236 መደበኛ ፖሊሶች አስመረቀ

71
አምቦ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2012 የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የመደበኛ ፖሊስና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል ለ28ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 236 መደበኛ ፖሊሶች አስመረቀ። ዛሬ ለምረቃ የበቁት ሰልጣኞች ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ መሆናቸው ተመልክቷል። የማሰልጠኛ ማዕከሉ ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ጉመሮ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ለምረቃ የበቁት የፖሊስ አባላት በስልጠና ቆይታቸው በመደበኛ ፖሊስ እና በህገ መንግስት ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል። የጦር መሳሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ በ11 የተለያዩ የትምህርት መስኮች በተግባር የተደገፈ ስልጠናም ወስደዋል። ስልጠናቸውን አጠናቀው ዛሬ የተመረቁት የፖሊስ አባላት ስነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ የህብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና በበኩላቸው የክልሉ ፖሊስ የህብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታን የማረጋገጥ ተልዕኮ ለማሳካት በተጠናከረና በተደራጀ አግባብ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ምሩቃን ፖሊሲች ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባና የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በሚሰሩበት አካባቢ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት ለትግል ጫካ የገቡ አካላት ትጥቅ ፈትተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉም ኮማንደር ጌታቸው ጥሪ አቅርበዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ከምዕራብ ጉጂ ዞን የመጣው ኮንስታብል ቂልጣ ሮቤ በሰጠው አስተያየት ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆን ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልግል መዘጋጀቱን ተናግሯል። ከምእራብ ሐረርጌ የመጣው ሌላው ተመራቂ ኮንስታብል ቃሲም አህመድ በበኩሉ " የወሰድኩትን ትምህርት በተግባር በመተርጎም ኃላፊነቴን በአግባቡ ለመወጣት ተዘጋጅቺያለሁ" ብሏል፡፡ ተመራቂዎቹ በተማሩበት የፖሊስነት ሙያ በቅንነት ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን በምረቃው ላይ አረጋግጠዋል። በምረቃው ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም