በጌዴኦ ዞን 6 ሺህ ለሚጠጉ ህፃናትና እናቶች ነፃ የህክምና አገልግሎት ተሰጠ

76
ዲላ ኢዜአ ህዳር 06/2012  በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳና አካባቢው ጆይስ ማዬር የተሰኘ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት 6 ሺህ ለሚደርሱ ህጻናትና እናቶች ነጻ የህክምና አገልግሎት መስጠቱን ገለፀ ። በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳና በአከባቢው ለሚገኙ ሴቶችና ህጻናት ነፃ የህክምና አገልግሎቱ የተሰጠው ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ላለፉት አምስት ቀናት በዘመቻ በሰጠው ህክምና ነው ። በኢትዮጵያ የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ዶክተር በረከት ዮሐንስ ለኢዜአ እንደገለፁት የነጻ ህከምና አገልግሎቱ ጆይስ ማዬር የተሰኝ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከቤተ ሳይዳ የህጻናትና እናቶች ህክምና ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው ። በመርሀ ግብሩም ጠቅላላ ህክምና ፣ የቆዳ ፣ የአይንና መለስተኛ ቀዶ ጥገናን ጨምሮ በ10 የህክምና አገልግሎት ዓይነቶች ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል ። አገልግሎቱ የመድሃኒት አቅርቦት ፣ የመነጽርና የሌሎች አጋዥ ቁሳቁሶች ስርጭትጭምር ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል ። በአገልግሎቱም ከተለያዩ የአለም ሃገራት የተሰባሰቡ 36 ስፔሻሊስት ሃኪሞችን ያቀፈ የህክምና ቡድንን ጨምሮ 50 የሚደርሱ የሀገር ውስጥ ሃኪሞችንና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ተሳታፊ ሆነዋል ። የህክምና አገልግሎቱን በቀጥታ ካገኙ 6 ሺህ እናቶችና ህፃናት በተጨማሪ የራጅ፣ አልትራ ሳውንድ፣ ኤም አይ አርና መሰል ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው 50 ሰዎችም በድርጅቱ ሙሉ ወጭ ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ተልከው እዲታከሙ መደረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል። የአለም አቀፍ ህክምና ቡዱኑ አባል ዶክተር ኔሲ ጆንሰን በሰጡት አስተያየት በሙያቸው የጥርስ ሃኪም መሆናቸውን ጠቅሰው በሁሉም አገልግሎቶች በየቀኑ በአማካይ ከ800 ለሚበልጡ ታካሚዎች አገልግሎቱ መሰጠቱን ተናግረዋል። የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ነጻ ድጋፍ በማድረጋቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ለወደፊቱም ተመልሰው በመምጣት ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብለዋል ። አስተያየታቸው ከሰጡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ አልማዝ ዘሪሁን እንዳሉት ለበርካታ ጊዜያት ጀርባቸው ላይ የማቃጠል ህመም ይሰማቸውት እንደነበር በመግለፅ ህክምናው በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። ከራሳቸው በተጨማሪ ሁለት ልጆቻቸው ቆዳ ላይ ይታይ የነበረውን ሽፍታ በማስመርምር መድሃኒት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው ለተደረገው የነጻ የህክምና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው በዞኑ የህጻናትንና እናቶችን ጤና ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት አጋዥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም