በትግራይ የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

70
ህዳር 06/2012 ዓ.ም መቐለ ኢዜአ- ..... በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የትግራይ ክልል ከጎበኙ የውጭ ዜጎች 23 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን የክልሉ ቱሪዝምና ባህል ቢሮ ገለፀ ። ለጎብኚዎች ቁጥር መጨመር የነቃ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ቢሮው አስታውቋል ። የትግራይ ክልል የቱሪዝምና ባህል ቢሮ የገበያና ማስታወቂያ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዮናስ ታደለ እንደገለፁት በህዝብ የነቃ ተሳትፎ የክልሉ መስህብ ቦታዎችን በማስተዋወቅ በመጀመሪያው ሩብ በጀት ዓመት ብቻ 17 ሺህ የውጭ ዜጎች በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል ። ክልሉን ከጎበኙ የውጭ ቱሪስቶችም ከ23 ሚልዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ወደ ክልሉ ኢኮኖሚ መግባቱን ባለሙያው ተናግረዋል ። በክልሉ የጎብኚዎች ፍሰት ከአመት ወደ አመት እየጨመረ መጥቷል ያሉት ከፍተኛ ባለሙያው በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው ተቋማትና መላው የክልሉ ህዝብ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ ያደረጉት ጥረት የላቀ እንደነበር ገልፀዋል ። ባለሆቴሎችና አስጎብኚዎችም ክልሉን ለማስተዋወቅ እያደረጉት ጥረትም የሚደነቅ ነበር ብለዋል ። ከሶስት ዓመት በፊት 65 ሺህ የነበረው አመታዊ የጎብኚዎች ቁጥር በ2011 ዓ.ም የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ከ90 ሺህ በላይ  መድረሱን ተናግረዋል። በክልሉ ያለው አስተማማኝ ሰላም እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የጎብኚዎች ቁጥር ከመጨመሩም በላይ ቆይታቸው እንዲራዘም ማስቻሉንም አቶ ዮናስ ገልፀዋል። በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ገርዓልታ በተባለው አካባቢ የሚገኘው የቆርቆር  ሎጅ ስራ አስኪያጅ ሚስተር አንጀሎ ዴቫንዲ እንደገለጡት የተቀናጀ ስራ በመሰራቱ በአካባቢው የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የክልሉ መንግስት የቱሪዝም ሃብትን ለማስተዋወቅ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በአካባቢው ያሉት የሎጅ ባለቤቶች ሃብቶቹ በተለያዩ የአለም አገራት እንዲተዋወቁ እየሰሩ መሆናቸውን ነው ሚስተር አንጀሎ የተናገሩት። ከጥቂት አመታት በፊት ከአክሱም ቀሳውስትን ወደ ጄኔቫ በመውሰድ የአካባቢያቸውን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ለማስተዋወቅ የሰሩትን ስራ አንዱ ምሳሌ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ጨምሮው ጠቅሰዋል። ባለፈው ዓመት ክልሉን የጎበኙት 91ሺህ 764 የውጭ ጎብኚዎች የነበሩ ሲሆን ዘንድሮ ወደ 100 ሺህ የውጭ ቱሪስቶችን ለማሳደግ  አቅዶ እየሰራ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም