ፍትሃዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦትና ስርጭት እንዲኖር ንግድ ሚኒስቴር ቁጥጥር ማድረግ አለበት ተባለ

1128

አዲስ አበባ ሰኔ13/2010 በአገሪቷ ፍትሃዊ የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦትና ስርጭት እንዲኖር ንግድ ሚኒስቴር በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና አከፋፋዮች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድ ሚኒስቴርን የ2010 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ገምግሟል።

ባለፉት 11 ወራት  ከአምስት ሚሊዮን 860 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ 4 ሚሊዮን 279 ኩንታል ስኳር እና 376 ሚሊዮን 256 ሺህ ሊትር ፓልም የምግብ ዘይት መሰራጨቱ ተገልጿል።

ይህም በበጀት ዓመቱ ለማሰራጨት ከታቀደው አንፃር ሲታይ አፈፃፀሙ  ስንዴ 94 ነጥብ 68 በመቶ፣ ስኳር 62 ነጥብ 15 በመቶ እንዲሁም የምግብ ዘይት 85 ነጥብ 51 በመቶ ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘውዱ ከበደ በአገሪቷ መንግስት የሚያስገባቸው መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በአግባቡ ለኅብረተሰቡ ባለመድረሳቸው “በዝቅተኛ ኢኮኖሚ የሚተዳደሩ ዜጎች እየተጎዱ ነው” ብለዋል።

እነዚህ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ሙሉ በሙሉ ካለመሰራጨታቸውም ባለፈ “ስርጭታቸው ፍትሃዊነት የጎደለው፤ በተገቢው ጊዜ ለኅብረተሰቡ የማይደረሱ መሆናቸውንም በተለያዩ አካባቢዎች አረጋግጠናል” ብለዋል።

ይኸውም የንግድ ሚኒስቴር የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና አከፋፋይ ነጋዴዎች በቅርበት ተናበው መስራታቸውን በአግባቡ ስለማይቆጣጠር መሆኑን አስረድተዋል።

የፍጆታ እቃዎች ከተቀመጠላቸው የዋጋ ተመን በእጥፍ የሚቸበቸቡት፣ ለኅብረተሰቡ በወቅቱ የማይደርሱትና ስርጭታቸው ፍትሃዊነት የጎደለው በአሰራር ክፍተት መሆኑን አስረድተዋል።

“በአንዳንድ የኅብረት ስራ ማህበራት የተከማቸ ዘይት ወይም ስኳር እያለ በዚያው አካባቢ ሸማቹ ማኅበረሰብ በፍጆታ እቃዎች እጥረት ሲማረር አስተውለናልም ነው” ያሉት።

ንግድ ሚኒስቴርና በዘርፉ ያሉ አደረጃጀቶች የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና ነጋዴዎች አገልግሎቱን በአግባቡ እንዲሰጡ በቅርበት መቆጣጠር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ችግሮች እንዳሉ አምነው፤ የስርጭቱ በአሰራር የሚስተካከል ቢሆንም “አቅርቦቱ ግን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚፈታተን ነው” ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመከላከል ከሸማቾች ኅብረት ስራ ማህበራትና አከፋፋይ ነጋዴዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይም እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

ሸማቹ ማኅበረሰብም ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ለመንግስት በማሳወቅ ለፍትሃዊ የንግድ ስርዓቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።