ዓመታዊ የወንድና የሴት የበረሃ የብስክሌት ውድድር በመቀሌ ተካሄደ

59
መቀሌ (ኢዜአ) ህዳር 5/ 2012 -በመቀሌ በተካሄው ዓመታዊ የወንድና የሴት የበረሃ የብስክሌት ውድድር መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ እና ብሩህ ተስፋ ክለቦች አሸነፉ። በሁለቱ ጾታዎች ዳገትና ቁልቁለት የበዛበት የኮርስ ውድድር የተካሄደው ከመቀሌ እስከ ሃገረ ሰላም ተምቤን ደርሶ መልስ ነው። በሴቶች መካከል በተካሄደ የ80 ኪሎ ሜትር የበረሃ የኮርስ ብስክሌት ውድድር የመስፍን ኢንጂነሪንግ ተወዳዳሪዎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል። የውድድሩ ዋና ዳኛ አቶ ተስፋይ አማረ እንዳሉት በውድድሩ 12 ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ዳገትና ቁልቁለት የበዛበትን ርቀቱ ለመጨረስ በሰዓት 31 ኪሎ ሜትር በመጓዝ በአጠቃለይ 2 ሰዓት ከ34 ደቂቃ ፈጅቷል። በውድድሩ መሰረት መብራት ግዛው፣ ነፃነት ግርማይና ዛይድ ሃፍቱ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ከመስፍን ኢንጂነሪንግ ተከታትለው በመግባት አሸናፊ ሆነዋል። በአጠቃላይ 32 ብስክሌተኞች በተሳተፉበትና 160 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የወንዶች የበረሃ ውድድርም የብሩህ ተስፋ ተወዳዳሪ አሽንፏል። ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ሲሆን ታምራት መረሳ ከብሩህ ተስፋ ክለብ ቀዳሚ ሆኗል። ሃፍቶም አዳነ ከመሰቦ ክለብ ሁለተኛ፣ ገብረመድህን ገብረእግዚአብሔር ከብሩህ ተስፋ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል። ብስክሌተኞቹ የውድድሩን ርቀት ለመጨረስ በሰዓት 32 ኪሎ ሜትር በመጋለብ በአጠቃላይ 4ሰዓት ከ45 ደቂቃ የፈጀባቸው መሆኑ ዋና ዳኛው አቶ ተስፋይ ተናግረዋል። ውድድሩ በዘርፉ ብቁና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት አልሞ የተካሄደና ተስፋ ያላቸው ስፖርተኞች የታዩበት መሆኑን አቶ ተስፋይ አያይዘው ገልጸዋል ሲ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም