በገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው ውጤታማ ለሆኑት እውቅና ተሰጠ

86
(ኢዜአ) ህዳር 5 / 2012 … በገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር ተደራጀተው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ሴቶች ውጤታማ በመሆናቸው ኑሯቸው መለወጡን ገለጹ። "ጀግኒት ትቆጥባለች" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር ተደራጀተው ውጤታማ ለሆኑ ማህበራት ዛሬ በአዳማ ከተማ ዕውቅና ተሰጥቷል። ከትግራይ ክልል ኮረም ከተማ የመጡትና "ኪዳነ የገንዘብ ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር" አባልና ሊቀመንበር የሆኑት ወይዘሮ ደብሬ መለስ እንደገለጹት በገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበር ከመደራጀታቸው በፊት ለዘመናት በችግር አሳልፈዋል። "በማህበር ተደራጀተን ባገኘነው የገንዘብ ብድር በእንስሳት እርባታ፣ በአነስተኛ ንግድና በአገልግሎት የሥራ ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ በመሆናችን ኑሯችንን መለወጥ ችለናል" ብለዋል። ወይዘሮ ደብሬ እንዳሉት ማህበሩ 60 አባላት ያሉት ሲሆን አባላቱ በተለያዩ መስኮች ሥራ የጀመሩት ባዋጡት 20 ሺህ ብር የመነሻ ከፒታል ነው። "ማህበሩ ከትግራይ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በትብብር እየሰራ ነው" ያሉት ሊቀመንበሯ፣ የአባላቱን የንግድ እንቅስቃሴና የገንዘብ አቅም ለማሳደግ በተደረገ ጥራት ባለፈው ዓመት ለእያንዳንዱ አባላት 50ሺህ ብር ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የማህበሩ ካፒታል 5 ሚሊዮን ብር መድረሱን ጠቁመው፣ በዘንድሮ ዓመትም ለአባላቱ በነፍስ ወከፍ 100ሺህ ብር ብድር በመሰጠት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። "በማህበር ተደራጅቼ ባገኘሁት የገንዘብ ብድር በአነስተኛ የንግድ ሥራ ላይ በመሰማራት በጥሬ ገንዘብ 300 ሺህ ብር በባንክ አስቀምጫለው" ያሉት ደግሞ በድሬደዋ ከተማ "የቀጠና ሁለት ሚካኤል የሴቶች ብድርና ቁጠባ ማህበር " አባል ወይዘሮ ዘይቱና አረቢ ናቸው። ተደራጀተው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በኪራይ ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ገለጸው ሰርተው ውጤታማ በመሆናቸው በድሬዳዋ ከተማ የራሳቸውን መኖሪያ ቤት ከመስራት ባለፈ ልጆቻቸውን እስከ ዩኒቨርሲቲ አስተምረው ለሥራ ማብቃታቸውን ተናግረዋል። "በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ብድር ከማህበሩ ለመውሰድ የገበያ ጥናት እቅድ አቅርቢያለሁ" ያሉት ወይዘሮ ዘይቱና፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ማቀዳቸውን ገልጸዋል። የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጠናከር በልማቱ ንቁ ተሳታፊ ከማድረግ ባለፈ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን ማስፋት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ የዓለም ፀጋይ ናቸው። የተሻለ አቅም የፈጠሩ ሴቶች በአራጣ አበዳሪዎች እንዳይበዘበዙ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማስፋፊያ ተቋማትን አቅም ማጠናከርና የሴቶችን የቁጠባ ባህል ማደባር የበጀት ዓመቱ ትኩረት መሆኑን አስታውቀዋል። እንደሚኒስትሯ ገለጻ ባለፈው የበጀት ዓመት ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች በሕብረት ሥራ ማህበር ተደራጀተው ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ቆጥበዋል። የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር በበኩላቸው ሴቶች በልማቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ከኢኮኖሚዊ ዕድገቱ በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል። በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት በህብረት ሥራ ማህብራት አዋጅ፣ አደረጃጀት፣ አሰራርና ጠቀሜታ ላይ ሴቶች በቂ እውቀት እንዲያገኙ የአቅም ግንባታ ሥራ በዘላቂነት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በአዳማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የእውቅና አሰጣጥ መርሀግብር ላይ ከዘጠኙ የአገሪቱ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 120 የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበራት የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል  ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም