በየሆስፒታሉ ያሉ ታማሚዎች የመንፈስ ድጋፍ እንዲያገኙ የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ተባለ

53
አዲስ አበባ  ሰኔ 13/2010 በየሆስፒታሉ ያሉ ታማሚዎች ከሚሰጣቸው የህክምና አገልግሎት ባሻገር የመንፈስ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የሃይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። "አክብሮት፣ ርህራሄና ስነ-ምግባር በተላበሰ አገልግሎት ህሙማንን የመጠየቅ ሳምንት" በሚል መሪ ሃሳብ በየሆስፒታሉ የሚገኙ ታማሚዎችን የመጠየቅ ሳምንት ከሰኔ 11 እስከ 15 እየተካሄደ ነው። ይህንንም አስመልክተው የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ዛሬ በአለርት የህክምና ማዕከል በመገኘት አካል ጉዳተኞችን፣ የስጋደዌ፣ የቲቢ እንዲሁም የድንገተኛ ታካሚዎችንና የወለዱ እናቶችን ጎብኝተዋል። የሃይማኖት አባቶቹ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን የተውጣጡ መሆናቸው ተገልጿል። የጤና ጥበቃ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ጌታቸው አሸናፊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት "በመንፈስ የጠነከረ ታካሚ ከህመሙ የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው"። በየሆስፒታሉ ያሉ ታማሚዎች የጤና ሙያተኛው ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ባሻገር ርህራሄና ክብር በተሞላ አግባብ እንዲገለገሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህም በተለይ የሃይማኖት አባቶች ታማሚዎች መንፈስ ጠንካራ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶቹ በበኩላቸው የኢትዮጵያውያን የመተባበር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባህላቸው ሊጎለብት እንደሚገባ ጠቁመዋል። "የሰው ልጅ ክብርና ርህራሄ ሊኖረው ይገባል" ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ የተቸረገን የመርዳትና የታመመን የመጠየቅ ተግባር የሁሉም ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል። ህብረተሰቡ አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ በተለይም የትራፊክ አደጋና መሰል ችግሮች ተጋላጭ እንዳይሆንም በየሃይማኖት ተቋማታቸው አስተምህሮት እንደሚሰጡም ተናግረዋል። በመሆኑም በተለያዩ የጤና ተቋማት የሚገኙ ህሙማን መንፈሰ ጠንካራ እንዲሆኑ ትምህርት የመለገስና የመጠየቅ ተግባራቸውንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም