ለሃገሪቱ ሰላምና አንድነት መጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

69
ጎንደር ሰኔ 13/2010 ለሃገራችን ሰላምና አንድነት መረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጀመሩት የለውጥ ጉዞ መሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የማራኪ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አበባ አዳነ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ያከናወኗቸው ተግባራት የህዝቡን አንድነትና ፍቅር የሚያጠናክሩና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ናቸው። “በጎንደር ከተማ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ የተረጋጋ ሕይወት መምራት ችሏል” ያሉት ወይዘሮዋ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግልጸኝነት አመራር ያመጣው ለውጥ በመሆኑ እደግፈዋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የፖለቲካ አስተሳስብ አፍላቂ በመሆናቸው ከጎረቤት ሀገሮች ጭምር መልካም ጉርብትና እንዲኖረን አዲስ የታሪክ ምእራፍ እንዲከፈት አድርገዋል” ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 18 ነዋሪ ሻለቃ ሰለሞን በላይ ናቸው፡፡ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ጭምር በመሄድ ኢትዮዮጵያውያን አስረኞችን አስፈትተው ለሀገራቸው ማብቃታቸውና ኢኮኖሚያዊ ትስስራችንን ለማጠናከር የወደብ ድርሻ ጭምር እንዲኖረን ያካሄዱት ዲፕሎማሲያዊ  ጥረት የአመራር ብቃታቸውን የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል። “በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር በማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጡዋቸው በሳል ምላሾችም ህዝቡን ያረኩና ለለውጥ ጎዞው ተስፋ የሚጣልባቸው መሪ በመሆናቸው ድጋፌን አስጣለሁ” ብለዋል። በሃዋሳ አካባቢ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ በትናንትናው እለት ቦታው ድረስ ፈጥነው በመሄድ ህዝቡን በማነጋገርና ተጎጂዎችን ጭምር በአካል በመጎብኘት ላደረጉት የማረጋጋት ስራ  ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው ጠቁመዋል። “በቁርጥ ቀን የደረሱ ብልህና አስተዋይ መሪ በመሆናቸው ታላቅ የህዝብ ድጋፍ የሚቸራቸው የነገ ተስፋ ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸው” በማለት የተናገሩት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 6 ነዋሪ የሆኑት አቶ አድማሴ ደሞዝ ናቸው። “ከሰላም የበለጠ ምንም ነገር የለም ባለፉት ሁለት ወራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌት ተቀን በመሯሯጥ ከዳር እስከ ዳር የሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉት አስተዋጽኦ ታላቅ ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ የአልጀርሱን ስምምነት ለመተግበር የተላለፈው ጥሪ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ሰላም የሚያወርድ በመሆኑ የሚደገፍ መሆኑንም ጠቁመዋል። መላው የከተማችን ህዝብ ከጎናቸው መሆናችንን ማረጋገጥ እንፈልጋለን ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በአዲስ አበባ በመጪው ቅዳሜ የተዘጋጀውን የምስጋና የድጋፍ ሰልፍ እንደሚደግፉትም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም