ጤና ሚኒስቴር የጤና ባለሙያዎችን የአለባበስ ስርዓት መመሪያ ይፋ አደረገ

309

አዲስ አበባ ህዳር 5/2012  የጤና ሚኒስቴር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የጤና ባለሙያዎች የአለባበስ ስርዓት መመሪያን ይፋ አደረገ።

በመመሪያው መሰረት አምስት አይነት የአለባበስ ስርዓት በሁሉም የጤና ተቋማት የሚተገበር ሲሆን በሦስት የሙያ አይነትና በሁለት የአገልግሎት ዘርፍ የተለየ ቀለም የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል። የአለባበስ ስርዓቱ የድንገተኛ፣ የስነ ተዋልዶ፣ የቀዶ ጥገናና ጽኑ ህሙማን አገልግሎት ዘርፍ ተለይቶ የቀመጠ ሲሆን፤ እንዲሁም የሐኪሞችና የነርሶችም በተለያየ ቀለማት የተዘጋጀ ነው። የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻል የተለያዩ የለውጥ ስራዎች እየተተገበሩ ይገኛሉ። ስለሆነም ምቹ የሆነ የአለባበስ ስርዓት በጤና ተቋማት ላይ መዘርጋት አንዱና ዋነኛው ነውም ብለዋል ሚኒስትሩ። በየሆስፒታሎች አንሶላና ብርድልብስን ጨምሮ የባለሙያዎች መለያ ያለው አልባሳትን ለማሟላት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚቆይ ኮንትራትም ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጋር ስምምነት እንደሆነም ዶክተር አሚር ገልጸዋል። የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የጤና ባለሙያዎች የአለባበስ ስርዓት በሁሉም ጤና ተቋማት ከጥር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደርግም ገልጸዋል። የጤና ባለሙያዎችን የአለባበስ ስርዓት በጤና ተቋማት ውስጥ ወጥ ማድረግ፣ ተገልጋዩ ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጠውን ባለሙያ ማንነት በቀላሉ እንዲያውቅ እንደሚያግዝም ተናግረዋል። በተጨማሪም የጤና አገልግሎት አሰጣጡ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው የአለባበስ ስርዓቱ ወጥና ልዩ መሆኑ ተገልጋዩ ሳይገላታ በአግባቡ እንዲስተናገድና ለባለሙያው ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። ሲስተር ጥሩወርቅ አክሌ በሰጡት አስተያየት በጤና ተቋማት የሚያገለግሉ ባለሙያዎች እንዲሁም ተገልጋዮችን ከተላላፊ በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠርም ንጽህናውን የጠበቀና ስርዓት ያለው ሙያዊ አለባበስ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል። ቀደም ሲል የነበረው የጤና ባለሙያዎች አለባበስ ከሌሎች ሙያተኞች ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑም ሐኪሞችን ለመለየት አስቸጋሪ እንደነበር ያወሳሉ። ይሁን እንጂ የራሱ የሆነ የአለባበስ ስርዓት መበጀቱ ከሌሎች የሙያ ዘርፎች በቀላሉ እንዲለይ ያስችላልም ብለዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ ዶክተር መኮነን አስረስ በበኩሉ የጤና ባለሙያዎች የአለባበስ ስርዓት የባለሙያውን ሙያዊ ገጽታ በመገንባትና ክብር እንዲሰማው ለማድረግም ያግዛል። እንዲሁም ተገልጋዩ ማህበረሰብ በሚገለገልበት ተቋምና በሚያገለግለው ባለሙያ አመኔታውን ለማሳደግም ያገግዛል ተብሏል። የባለሙያው አለባበስ የተለየ መሆኑ የህክምና ተገልጋዩ በቀላሉ መረጃዎችን እንዲያገኝና ቀልጣፋ አገልግሎት በማግኘትም ጊዜና ጉልበቱን እንዲቆጥብ ያስችለዋል ብለዋል። አዲሱ የአለባበስ ስርዓት በኢትዮጵያ በሚገኙ በሁሉም የመንግስት፣ የግልና የግብረሰናይ የጤና ተቋም ውስጥ በሚሰሩ ባለሙያዎችና ተማሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም