የመቀሌ ከተማን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞች ለብክለት መጋለጣቸውን ነዋሪዎች ገለፁ

69
ህዳር 05/12 መቀሌ ኢዜአ --የመቀሌ ከተማን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞች ተገቢውን ጥበቃ ስለማይደረግላቸው ለብክለት እየተዳረጉ መምጣታቸውን የከተማው ነዋሪዎቹ የገለጹት። የከተማው ግብርና ፅህፈት ቤት በበኩሉ ብክለቱን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጿል። በከተማው በግብርና ልማት ስራው ከተሰማሩ ነዋሪዎች መካከል አቶ ገብረመድህን እንግዳ በሰጡት አስተያየት ላለፉት አራት ዓመታት የወንዝ ውኃን በመጠቀም በሩብ ሔክታር መሬት ላይ በመስኖ ቲማቲም እያመረቱ ለገበያ ሲያቀርቡ ነበር ። በዓመት በአማካይ 50 ኩንታል ቲማቲም በማቅረብ ኑሮአቸውን ይደጉሙ እንደነበር ገልፀው የወንዞቹ መበከል ግን በከተማ ግብርና ስራቸው ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል ። ከተማውን አቋርጠው በሚያልፉ ወንዞች ላይ የሞቱ የቤት እንስሳትና ደረቅ ቆሻሻ እንደሚጣልበትና በብዛት መኪኖች ስለሚታጠብበት ውኃው ተበክሎ ምርታማነቱን እንደቀነሰው አስረድተዋል ። በከተማው በተለምዶ ‘’ዓዲ ሓቂ ገበያ’’ እየተባለ በሚጠራው የከተማው መሃል አቋርጦ የሚያልፈው የወንዝ ውሃ በሰውና እንስሳት ሽንት፤ከሆቴሎችና ምግብ ቤቶች በሚጣለው ደረቅ ቆሻሻ ምክንያት ውሃው ስለተበከለ ለግብርና አገልግሎት የሚውል አይደለም ያሉት አቶ ሰለሞን መብራህቱ የተባሉ የልማቱ ተሳታፊ ናቸው ። የሚተክሉዋቸውን የጓሮ አትክልቶች እየተበላሹ መቸገራቸውንም ተናግረዋል ። ወንዙን እንዳይበከል የሚከላኩሉ መልእክቶችን የያዙ ምልክቶች በየቦታው ብንተክልም ሰሚ አጥተናል ያሉት ደግሞ በተመሳሳይ የልማት ስራ የተሰማሩ በከተማው የቀበሌ 11 ነዋሪ አቶ ሙሉ ደስታ ናቸው። በወንዞቹ ዳርና ዳር ‘’መሽናት ክልክል ነው!ቆሻሻ የደፋ ይቀጣል አትክልት መርገጥና አጥር መዝለል የተከለከለነው !’’ የሚሉ የማስጠንቀቂያ መልእክቶች የያዙ ታፔላዎች ቢተከሉም ከቁምነገር የሚቆጥራቸው ሰው እንደሌለና የወንዞቹ ብክለት መባባሱን ተናግረዋል። አቶ ሙሉ ደስታ እንዳሉት ባላቸው ግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ለስምንት ዓመታት ያህል  ቆስጣ፣ሰላጣና ድንች በማልማት በየዓመቱ በአማካይ 200 ኩንታል ምርት ለገበያ ሲያቀርቡ እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ግን በብክለቱ ምከንያት የጓሮ አትክልቶች መብቀል ወደ ማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ገልጸዋል። በመቀሌ ግብርና ጽህፈት ቤት የግብርና ኤክስቴሽን አስተባባሪ አቶ አሸብር አብርሃ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት የከተማው መሃልና አዋሳኝ ቦታዎች አቋርጠው የሚፈሱ ወንዞችና ምንጮችን በመጠቀም ከ675 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት ተችሎ ነበር ። በልማት ስራውም 2ሺህ 500 ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረጉን የገለጹት አስተባባሪው በአሁኑ ጊዜ ግን በወንዞቹ እየደረሰ ባለው ብክለት ምክንያት የሚፈለገውን ምርት ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል። የወንዞቹ ብክለት ለመከላከልም ከአካባቢ ጥበቃ፣የፅዳትና ውበት ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር የክትትልና ቁጥጥር ስራ በማድረግ ላይ ነን ብለዋል ። ቦታዎቹ በቀጣይነት ለማፅዳት ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት በወንዙ ዳር ቋሚ ተክሎች አልምተው እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በከተማው ማዘጋጃ ቤት የአረንጓዴ ልማትና የከተማ ፅዳት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሞጎስ ፋንታዬ በበኩላቸው በከተማው ከሚገኙ 14 ተፋሰሶች መካከል በስፋት ቆሻሻ የሚጣለባቸው ቦታዎችን በጥናት ተለይተው ህብረተሰቡን በማነቀነቅ በዘመቻ የማጽዳት ስራ ተጀምሯል ብለዋል። አንዳንዶቹም ለስራ አጥ ወጣቶች ተሰጥተው ለመዝናኛ እንዲውሉ የማስዋብ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል። በወንዞቹ ዳር ተሽከርካሪዎች በማጠብና ቆሻሻ በመድፋት ብክለት የሚያስከትሉ ግለሰቦችም በህግ ፊት እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ መጀመሩን አስረድተዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም