ኢትዮጵያና ቻይና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

103

አዲስ አበባ ህዳር ዐ4/2ዐ12 /ኢዜአ/ ኢትዮያጵና ቻይና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓታቸውንና አጠቃላይ ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የቻይና የጉምሩክ አስተዳደር ሚኒስትር  ኒ ዩፌንግ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል የሚደረጉ የእውቀትና መረጃዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርና በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነትና ትብብር ለማጠናከር እንደሚረዳ ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ስምምነቱ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓትን እንዲሁም አጠቃላይ ንግድንና የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማሳለጥ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

''ወጪና ገቢ ምርቶችን በተመለከተ ከአገሮች ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል'' ያሉት ሚኒስትሯ፤ ቻይና ወደ ኢትዮጵያ በርካታ ምርቶችን የምትልክና ከኢትዮጵያም ምርቶችን የምትቀበል መሆኗን ገልፀዋል።

ስምምነቱ ከገቢና ወጪ ምርቶች የተሻለ ገቢ ለማግኘት፣ በጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚከሰቱ ዕፅ ማዘዋወርን የመሰሉ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

የቴክኖሎጂ ትብብር፣ የአቅም ግንባታና ልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም ሁለቱ አገሮች ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን በመጠቆም።

የቻይና የጉምሩክ አስተዳደር ሚኒስትር ኒ ዩፌንግ የኢትዮጵያና የቻይና የንግድ ልውውጥ መጠን 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከው ምርት እድገት እያሳየ መሆኑን ተናግረው ኢትዮጵያ የላከችው የለውዝ ምርት ከከዚህ ቀደሙ 500 እጥፍ በላይ እድገት ማሳየቱን በማሳያነት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ተወዳጅ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከው ቡና 78 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን አስረድተዋል።

ዛሬ የተደረገው ስምምነትም የሁለቱ አገሮች የጠነከረ የንግድ ትብብር ግንኙነት በጉምሩክ ረገድ ለመድገም እንደሚረዳ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት እ.አ.አ በ1970 የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የቻይና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም