የአፍሪካ የህጻናት ቀን በክልል ደረጃ ትናንት በሀረር ከተማ ተከበረ

98
ሐረር ሰኔ 13/2010 በህጻናት ላይ የሚደርሰውን የመብት ጥሰት በመቅረፍ የድጋፍና እንክብካቤ ስራዎችን ለማጎልበት በሚደረግ ጥረት የባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የሴቶችና ህጻናት ሚኒስትር ገለጹ። የአፍሪካ የህጻናት ቀን በክልል ደረጃ ትናንት በሀረር ከተማ ተከብሯል። በዚሁ ጊዜ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ፀጋይ እንደተናገሩት በአገሪቱ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትና ሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በዚህም በህጻናቱና ሴቶች ላይ እየታዩ ያሉት ጥቃቶችና በማህበረሰቡ ዘንድ እያስከተለ የሚገኘው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ በሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለዚህም አንዱና ዋንኛው ያለ እድሜ ጋብቻ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው ይህም ህጻናቱን ለውስብስብ ችግር እየዳረጋቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በህጻናት ላይ የሚከሰተው ያለ  እድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛትና ተያያዢ ጉዳቶችን ለመከላከልና መብታቸውንና ደህንነትን ለማረጋገጥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሐዲ በበኩላቸው የክልሉ መንግስትና ወጣት ማህበራት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር ውጤቱ የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ተግባሩ በየጊዜው ቅርጹን እየለዋወጠ መምጣትና ስራውን የአንድ አካል ብቻ አድርጎ የመውሰድ ችግር ዋነኛው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የጎዳና ህይወትን ለመቅረፍ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ያለ እደሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ክልሉ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በእለቱም ያለእድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛትና ተያያዝ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ክልል አቀፍ ፕሮግራም በጋራ ለመስራት ወርልድ ቪዝን ኢትዮድያ ከሐረሪ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። "ህጻናትን ከጎዳና ህይወት እንታደግ" በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዓል ላይ የክልሉ እንዲሁም የምዕራብ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን  የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችና ሴቶችና ህጻናት ተገኝተዋል፡፡ በእለቱም በክልሉ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ስራዎችና የየትምህርት ቤት የህጻናት ፓርላማ የሚያከናውኗቸው ስራዎች ተጎብኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም