በአዲስ አበባ የባለሃብቶች ፎረም ማቋቋሚያ መመሪያ ጸደቀ

85

ህዳር ዐ4/2ዐ12 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የባለሃብቶች ፎረም ማቋቋሚያ መመሪያ መፅደቁን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ብሩክ እስከዚያ እንዳሉት ፎረሙ ባለሃብቶች ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ከባለሃብቶች የሚነሱትን ጥያቄዎች በተናጠል ከመመለስ በተደራጀ መልኩ ለማስተናገድና ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት አሰራሩን የተሻለ ያደርገዋልም ነው ያሉት።

ከመሬት፤ ከመሰረተ ልማትና ከፋይናንስ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመነጋገርና መፍትሄ ለመስጠት የፎረሙ መቋቋም ተገቢ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በኮሚሽኑ አቅም ብቻ ከመንቀሳቀስ የባለሃብቶች መደራጀት ጠቃሚ መሆኑን በመጠቆም።

የባለሃብቶች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማስፋፋት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ለአብነትም ከውጪ የሚመጡ ቱሪስቶችና ባለሃብቶች የሚቆዩባቸው ጥራታቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ማስገንባት ተጠቅሷል።

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ የገቢ ምንጭ እንዲያሳድገው አቶ ብሩክ ጠቁመዋል።

ፎረሙ ህገወጥ ኢንቨስትመንትን ከማስቀረትና ወደ ህጋዊ መንገድ ለማምጣት እንደሚረዳም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ወይንሸት ዘሪሁን በማምረቻ፣ በማህበራዊና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የፎረሙ አባል መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ፎረሙ በከተማው የሚገኙ ባለሃብቶችን ችግር ከመቅረፍ አንጻር ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ምክትል ኮሚሽነሯ አብራርተዋል።

ለቴክኖሎጂ ሽግግር ዕድገት፣ የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስና የውጭ ምንዛሪን ለማሻሻልም ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ጠቁመዋል።

የተቆላ ቡና ወደ ውጪ የሚልከው 'ያ' የተሰኘው ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ዳግማዊ ኢያሱ እስካሁን ድረስ በኢንቨስትመንት የተሰማራ ባለሃብት በግሉ እንደሚንቀሳቀስ ተናግረዋል።

''መንግስትም በተደራጀ መልኩ የማስተናገድ አቅም አልነበረውም'' ብለዋል።

የፎረሙ መቋቋም ስራቸውን ቀላልና ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ከ48 ሺህ በላይ ባለሃብቶች መኖራቸውን ከኮሚሹኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም