የጤና ዘርፍ የመረጃ ልውውጥና ትስስር ማሻሻያ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

68
ህዳር 4/2012 የጤና ዘርፍ የመረጃ ልውውጥና ትስስር ማሻሻያ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ይፋ ሆነ። የጤና አገልግሎት በኢትዮያ የጤናውን ዘርፍ የመረጃ ልውውጥና ትስስር ለማሻሻል በቀጣይ አምስት አመት የሚተገበር የመረጃ ቴክኖሎጂ መርሃግብር ይፋ ሆነ። መርሃ ግብሩ 'ዲጂታል ሄልዝ አክቲቪቲ' የተሰኘ ሲሆን በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) እና ሌሎች የልማት አጋሮች የሚደገፍ መሆኑ ተገልጿል። መርሃግብሩ  ከ63 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል። መርሃ ግብሩ ይፋ በሆነበት ወቅት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንዳሉት፤ ከአራት አመት በፊት የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲቀረፅ የመረጃ አብዮት አንዱ አጀንዳ ነበር። በመረጃ አብዮት ዙሪያ በእነዚህ አመታት ከልማት አጋሮች ጋር በርካታ ስራዎች ሲከወኑ እንደነበር ገልፀው ከነዚህ አንዱ በሆነው የዲጂታላይዜሽን ስራ በርካታ የጤና ተቋማትን በብሮድባንድ ኢንተርኔት ማገናኘት መቻሉን ጠቅሰዋል። ለጤናው ዘርፍ የሚረዱ መተግበሪያዎች መሰራታቸውን ገልፀው የመረጃ ባህልን ለማሳደግም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። ኢንፎርሜሽን በማስተዳደር ሂደትም እንዲሁ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀው የዛሬው መርሃግብርም የዘርፉን የትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት አድርጎ የተሰራ ነው ብለዋል። መርሃግብሩ የተሰሩትን ስራዎች ለማጠናከርእና አዳዲስ ስራዎችን በመጨመር የመረጃ አብዮትን ከቴክኖጂ ጋር አያይዞ ከግብ ለማድረስ የሚረዳ መሆኑን ዶክተር አሚር አስረድተዋል። ኢትዮጵያና አሜሪካ በተለይ በጤናው ዘርፍ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን የገለፁት የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የተልዕኮ ዳይሬክተር ሲያን ጆንስ ናቸው። የዛሬው መርሃ ግብር በጤናው ዘርፍ ያሉ ሰዎች ያገኙትን እውቀት መረጃን ወደተግባር በመቀየር ከተጠቀሙበት የተሻለ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። መርሃ ግብሩ ግቡን እንዲመታ የመረጃ አጠቃቀም ባህልና የቴክኖሎጂ አመለካከት ላይ መስራት እንደሚገባና በዚህ ረገድም ከትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል። መርሃ ግብሩ የጤና ባለሙያዎችን፣ የፖሊሲ አውጪዎችን አቅም በማጎልበት የተሻለና ውጤታማ ስራ እንዲሰራ የሚረዳ መሆኑንም ገልፀዋል። ጆህን ስኖው ኢንክ' የተባለ ዓለም ዓቀፍ ድርጅትና ሌሎች የልማት አጋሮች ፕሮጀክቱን እንደሚያስፈሙ የተገለጸ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ የጤና ባለሙያዎችና የፖሊሲ አውጪዎች ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል። የጤና ባለሙያዎች ስልጠና አግኝተው ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ተጠቁሟል። ዩኤስኤይድ በየዓመቱ በኢትዮጵያ የጤና ዘርፉን ለመደገፍ እስከ 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያህል ወጪ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም