ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት ተመሰረተ

131
ኢዜአ ህዳር 4/2012፡ የምክር ቤቱ መስራች ጉባኤ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮች እንዲሁም የድሬዳዋና አዲስ አበባ ከንቲባ ተወካዮች በመስራች ጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል። ምክር ቤቱ ሕዝባዊ መሰረት ያለው ስፖርትን ማስፋፋት፣ስፖርት በኢኮኖሚው መስክ የሚጫወተውን ሚና ማጎልበት ላይ እንደሚያተኩር ተጠቅሷል። ባለድርሻ አካላትን ያካተተው ይሄው ምክር ቤት የስፖርት ልማትን፣ድጋፍና ክትትል በበላይነት የሚመራ ይሆናል ተብሏል። ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የክልልና ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽኖችና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣የአገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ፕሬዝዳንቶችን በአባልነት ያቀፈ ነው። የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት፣ ስፖርት ኮሚሽን ተጠሪ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።       የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤በስፖርቱ ዘርፍ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን ቢያደርግም አጥጋቢ ነበር ለማለት አያስደፍርም። በዚህም ተወዳዳሪ መሆን ሳይቻል መቆየቱን አስታውሰው ''ትላላቆቹ ስፖርተኞች ያወረሱንንና የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ስፖርቱን ወደተሻለ ደረጃ መምራት ይገባል'' ሲሉ አብራርተዋል። በአንዳንድ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ሰዎችን ከማዝናናት ይልቅ ግጭት ሲፈጠር እየተስተዋለ መሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢው ምስረታው እንደዚህ አይነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ ቃል የሚገባበት መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ በተለይም ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና ዘርፉን ማዘመን በቀጣይ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል። ''ምክር ቤቱ በተለይ አገራዊ አድነት እንዲጠናከር ትልቅ ኃላፊነት አለበት'' ያሉት ሰብሳቢው በየአካባቢው የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ማህበረሰቡን በማሳተፍ የዘርፉን እምቅ አቅም መጠቀም ይግድ ነው ብለዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፤ አገሪቱ እና ሕዝቡ ከስፖርት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል ምክር ቤቱ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አንስተው ምክር ቤቱ ወቅታዊ መሆኑን አመልክተዋል። ''በስፖርቱ ዘርፍ ድል፣ስኬትና አሸናፊነት ማለት አብሮነት፣ መረዳዳት ሕዝቦችን ማስተሳሰር ነው'' ያሉት ዶክተር ሂሩት ብሄራዊ ምክር ቤቱ መነቃቀፍ ሳይሆን መደጋገፍን የምናሳይበት ነው ሲሉም ገልጸዋል። በተለይም ስፖርቱ በዜጎች የአኗኗር ዘይቤ፣ፍልስፍናና አስተሳሰብ ላይ ሚናውን መጫወት ስለሚኖርበት የጋራ አቅጣጫዎች ይቀመጠበታል ብለዋል። አገር አቀፍ የስፖርት ዘርፍ ሪፎርም ፍኖተ ካርታም ይፋ ተደርጓል። ፍኖተ ካርታው በዕድሜው ልክ ያላደገውን ስፖርት ማሳደግና ማዘመን፣የስፖርት ፖሊሲ አፈጻጸም ክፍተቱን መሙላትና የአርሶና አርብቶ አደሩን ባህላዊ ስፖርቶች ማጎልበት ላይ ያተኮረ ነው።                                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም