የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ለአገሪቷ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም አዎንታዊ አንድምታ አለው - የፖለቲካ ፓርቲዎች

59
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው የሰላም ጉዞ ለሁለቱ አገራት ብቻም ሳይሆን ለቀጠናውም ጠቃሜታው የጎላ መሆኑን ለኢዜአ አስተያየት የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ። ፓርቲዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በፓርላማ ቀርበው ያቀረቡትን ሪፖርትና ለቀረበላቸው ጥያቄ ለሰጡት ምላሽ አዎንታዊ አተያይ እንዳላቸውም ነው ያረጋገጡት። ፓርቲዎቹ እንደተናገሩት መንግሥት በቅርቡ ለጎረቤት አገሯ ኤርትራ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የኤርትራ መንግሥት ተቀብሎ ልዑክ ለመላክ መወሰኑ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው። ውሳኔው በአዋሳኝ ድንበር አካባቢ ለሚገኙት ሕዝቦች የመሰረተ ልማትና ሌሎች ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅሞች ከማስገኘቱም በላይ፤ በጣምራ ለመልማትና ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላቸዋልም ብለዋል። ያም ብቻ ሳይሆን ሁለቱ አገራት ለወታደራዊ ተግባራት የሚያወጧቸውን ወጪዎች በመቀነስ በትብብር የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ጎን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ማብራሪያ በኅብረተሰቡ ላይ የነበረውን ብዥታ በማጥራት አገሪቷን ወደፊት የሚያራምድ መሆኑንም አስረድተዋል። በድምሩም ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተካሄዱት የለውጥ ሥራዎች ለአገሪቷ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ያለው አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ገብሩ በርሄ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት “ በዚያ አካባቢ ከሁለቱም መንግስታት የሚፈስ ነዋይና ሃብት ለሰራዊት ቀለብም ሆነ ለሎጂስቲክ የሚወጣው ገንዘብ ለሌላ ልማት እንዲውልም ያደርጋል። ስለዚህ የኤርትራ መንግስት ልኡካን እልካለሁ ብሎ መግለጫ ሰጥቷል ትናንት እኛ በአዎንታ ነው የምንቀበለው። ’’ አቶ ተሻለ ሰብሮ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት “ ለኢትዮጵያ ሴኩሪቲ ወሳኝ ነው፤ ያለቀለት የባድመ ጉዳይ በሰላም ባለቀ ቁጥር አርቀን የምናየው በዚያ አካባቢ ላይ በኢትዮጵያና በህዝቡ ላይ የሚመጣውን ችግር ተከላከልክ ማለት ነው፤ ትልቁን የቤት ስራ ተወጣህ ማለት ነው።’’ አቶ አየለ ጫሚሶ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት “ብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር ትልቅ ነገር ነው፤ ይህ ግን አገሪቱን ስታከብር ነው፤ ኢትዮጵያዊነትን ስታምን ነው።’’ በተለይም በአገሪቷ አንፃራዊ ሰላም ከማምጣት፣ የፖለቲካ ምህዳር ከማስፋትና ፍትህን ከማስፈን አንጻር የተጀመሩት ጥረቶች፣ እስረኞችን ከማስፈታትና ህዝብን ከማወያየት ረገድ በርካታ ለውጦች መታየታቸውንና ለውጤታማነታቸው ሁሉም ሰው ሊተባበር እንደሚገባም ገልፀዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም