ህንድ መድሃኒቶችን ለኢትዮጵያ ለገሰች

104
ኢዜአ ህዳር 4/2012፡ የህንድ መንግሥት ሁለት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸው የተለያዩ መድኃኒቶችን ለኢትዮጵያ ለገሰች። የተለገሰው መድኃኒት ከሁለት ዓመታት በፊት የህንዱ ፕሬዚዳንት ሽሪራም ናታ ኮቪንዳ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉት ወቅት የገቡትን ቃል ተከትሎ ነው ተብሏል። ፕሬዚዳንቱም አንድ ሺህ ሜትሪክ ቶን ሩዝ፣ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ መድኃኒቶችና 100 ሺህ የሒሳብና የሳይንስ መጽሃፍ ለመለገስ ቃል ገብተው ነበር። በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኑራግ ሰርቪስታቫ ትላንት ማምሻውን በኤምባሲያቸው በተዘጋጀው መርሃ-ግብር መድሃኒቶቹን ለጤና ሚኒስቴር አስረክበዋል። አምባሳደሩም በመልዕክታቸውም ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በጤና ዘርፍም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አጋርነትን እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁንም የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችና የትምህርት ድጋፍ፣ የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍና ኢትዮጵያዊያን በህንድ አገር የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። ለአብነትም ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሲቲ ስካን መሳሪያ ድጋፍ ማድረጋቸውንና በቅርቡም በአዲስ አበባ የአካል ጉዳተኞች የጤና ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት። በቀጣይም ህንድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን መሰል ድጋፎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደሩ ገልጸዋል። ህንድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ለአፍሪካ 10 ቢሊዮን ዶላር አነስተኛ ወለድ ያለው ብድር በአምስት ዓመታት ወስጥ ለማቅረብ ካቀረበችው መርሃ-ግብር ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ነች። በድጋፍ መልኩም ለልማት የሚውል 600 ሚሊዮን ዶላርና ለአፍሪካ ካቀረበችው 50 ሺህ ነጻ የትምህርት ዕድልም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ መሆኗ ተጠቅሷል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ የተደረገው ድጋፍ ህንድ ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ከምታደርጋቸው ድጋፎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል። ድጋፉም የበርካታ ሰዎች ህይወት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድርና ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠርም ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ህንድ ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታጠናክርና በተለይም በመድሃኒት ምርት ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት እንድትሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል። ህንድና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከመሰረቱ ከ70 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም