ስደተኞች በሚኖሩበት አካባቢ የተጎዳውን የተፈጥሮ ሀብት መልሶ ለማልማት እየተሰራ ነው

84
ኢዜአ ህዳር 4/ 2012  በትግራይ ክልል የስደተኛ ካምፖች ባሉበት አካባቢ ጉዳት የደረሰበት የተፈጥሮ ሀብት መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ 250 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የስደተኞች ተፅእኖ ምላሽ ልማት ፕሮጀክት ገለፀ። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሀይለኪሮስ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት የኤርትራ ስደተኞች በሚኖሩበት አካባቢ ማገዶን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የደን ውጤቶችን ስለሚጠቀሙ በተፈጥሮ ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል ። ተጽእኖውን ለመቀነስና አካባቢውን መልሶ ለማልማት በግብርና፣ትምህርት፣ጤና፣መንገድ ፣ውሃ፣ ኢነረጂና የአካባቢ ጥበቃ  ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። የአካባቢ የደን ውድመትን ለመከላከል በ905 ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማትና  የተለያዩ ስራዎች  ተከናውነዋል ። ፕሮጀክቱ  በአስገደ ጽምብላ፣በጸለምቲና ታህታይ አድያቦ ወረዳዎች  በሚገኙ 18 ቀበሌዎች የስደተኞች ተጽእኖ ምላሽ የተሰራባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። በፕሮጀክቱ 85 ሺህ 924 የኤርትራ ስደተኞችን ጨምሮ 239 ሺህ 759 የአካባቢው ነዋሪ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በዚህም ስደተኞቹ በሚኖሩባቸው አከባቢዎች  825 ሺህ 233 ችግኝ፣18  አነስተኛ የውሀ ማሰባሰቢያ ግድብ ፣48 መለስተኛ የመጠጥ ውሀ ጉድጓዶች ፣ 7ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የውሀ መውረጃ ቦይ ከተሰሩት የልማት ስራዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ። ከተፋሰስ ልማት ስራዎች  በተጨማሪ 15 ሺህ ኤርትራውያን ተማሪዎችን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች የሚማሩባቸው 35 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል። የጤና  አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የመጠጥ ውሀ አገልግሎት ጨምሮ 30 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጥርጊያ መንገድ የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል። ስደተኞቹና የአካባቢው ነዋሪዎች ለምግብ ማብሰያነት የሚጠቀሙት እንጨት በመሆኑ ብዙ የደን ሃብት ወድሟል ያሉት አቶ ሃይለኪሮስ ይህን ለመከላከል  84 ባዮጋዝ ጨምሮ በጸሀይ ብርሀን የሚሰሩ ሶላርና ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ማከፋፈላቸውን  ተናግረዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የፀለምቲና የአስገደ ፅብላ ወረዳ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአካባቢው የተጎዱ ቦታዎች የማዳን ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከአርሶ አደሮቹ መካከል የአስገደ ፅምብላ ወረዳ ስምረት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ሻምበል ገብረኪዳን እንዳሉት  ባለፉት ሁለት አመታት በአካባቢያቸው ተከታታይ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ ስደተኞቹ ባረፉበት አካባቢ የደን ውድመቱ በጣም ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው አሁን በተሰራው  ስራ መልሶ እያገገመ ነው ብለዋል ። ፕሮጀክቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች ከኤርትራውያን ወንድሞቻቸው ጋር አብረው እንዲማሩና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሎናል ያሉት ደግሞ በፀለምቲ ወረዳ  የመድሃኔአለም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዘርፌ ሃይለስላሴ ናቸው ። ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች በሚኖሩበት አካባቢ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ከአለም ባንክ በሚገኝ ብድር  የልማት ስራዎች የሚያከናውን መሆኑን ከአስተባባሪው ገለፃ ለማወቅ ተችላል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም