የኢንዶኔዥያ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ለማስተሳሰር እሰራለሁ --- አምባሳደር አልቡሽራ

74
/ኢዜአ / ህዳር 3/2012  የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሽራ የሀገራቸው ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለማስተሳሰር እደሚሰሩ ገለጹ። በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳንደር አልቡሽራ ባስኑር ወሎ ዩኒቨርሲቲን ከአገራቸው አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለማስተሳሰር ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዶኔዥያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሳር የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በኢንዶኔዥያ ከ700 በላይ የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸውን የተናገሩት አምባሳደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን የሚያጎለብቱ ቤተ ሙከራዎች ያሟሉ ናቸው  ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር መምህራንና ተማሪዎች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያጎለብቱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ አምባሳደሩ ገለጻ እስከ አሁን ድረስ ከአዲስ አበባ፤ ባህርዳርና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ ሲሆን መምህራንና ተማሪዎች የልምድ ልውውጥ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን ደግሞ ወሎ ዩኒቨርሲቲን ከአቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር በቴክኖሎጂ ሽግግር፤ በሰው ሀብት ልማት፤ በዲሞክራሲና ሰላም ዙሪያ በጋራ ለመስራት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም  የወሎ ሰላም፤ ፍቅር፤ አንድነትና መቻቻል ከአገራቸው ጋር እንደሚመሳሰል የገለጹት አምባሳደር አልቡሽራ ተማሪዎች አገራቸውን ለማሳደግ ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ እንዲሰጡ መክረዋል፡፡ በኢንዶኔዥያ ከ700 በላይ ቋንቋዎች፤ ከ7 በላይ እምነቶችና በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ቢኖሩም ተቻችለውና ተፋቅረው ሰላማቸውንና አገራቸውን አሳድገዉ ለአለም ምሳሌ መሆን እንደቻሉ አስረድተዋል ። ቀጣይ የኢንዶኔዥያ መምህራንና ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ደግሞ ወደ ኢንዶኔዥያ  ሔደው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ምሩቃን ተማሪዎችን ከኢንዱስትሪና ፋብሪካዎች ጋር በማስተሳሰር ስራ አጥነትን መቀነስ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው ከኢንዶኔዥያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመቆራኘት ያደረግነው ስምምነት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማጎልበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በኢንዶኔዥያ ያለውን ብዙ ልዩነት እንዴት አቻችለዉ ማደግ እንደቻሉም ተሞክሮ በመውሰድ ሰላም፤ አንድነትና ዲሞክራሲን ለማጎልበት ዩኒቨርሲቲው በጋራ እንደሚሰራ አስረድተዋል ። በተለይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የመውቂያና ማጨጃ ማሽን፤ ኬሚካል መርጫ፤ የመኖ ማቀነባበሪያና ሌሎች ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውን የገለፁት ዶክተር አባተ የፈጠራ ሰራቸውን ለማሳደግ ትስስሩ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል ፡፡ አምባሳደሩ የአገራቸውን እድገትና የዩኒቨርሲቲዎቻቸውን የመማር ማስተማር ሂደት ምን እንደሚመሰል ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ተማሪዎች ተሞክሮአቸውን አጋርተዋል፡፡ ከዉይይቱ ተሳታፊ ተማሪዎች መካከል የ4ኛ አመት የህግ ተማሪ  ሰይፉ ተስፋዬ በሰጠው አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ከኢንዶኔዥያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንዲተሳሰር መደረጉ የውጭ እድል ለማግኘት እንደሚጠቅም ገልጿል፡፡ አምባሳደር አልቡሽራ ዛሬ ከደሴና ኮምቦልቻ ከተማ ባለሃብቶች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም