የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል እየሰራሁ ነው አለ

136
ኢዜአ ህዳር 3/2012  ችግር ተፈጥሮባቸው በነበሩ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቋርጦ የነበረውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ለመመለስ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ዩኒቨርሲቲዎቹን አሁን ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ማምሻውን መግለጫ ሰጥቷል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በመግለጫቸው እንደጠቀሱት "በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረው ግጭት በተማሪዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሚማሩ ተማሪዎች ላይ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር።" ወልዲያ፣ ጅማ፣ መቱ፣ መዳወላቡና ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይስተጓጎል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በሌሎች አካባቢዎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምልክቶች እየታዩ በመሆኑ ችግሮቹን አስቀድሞ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለመመለስ ከአካባቢውና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ውይይቶች መቀጠላቸውን አስታውቀዋል። ችግር ፈጣሪዎቹ ተማሪዎች እንዳልሆኑና ተማሪ መስለው ወደ ግቢ በመግባት ጉዳቱን ማድረሳቸውን ጠቅሰው ከፌዴራልና ከክልል ፖሊሶች ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሰራ ነው ብለዋል። ''መንግስት የተማሪዎችን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ይህንኑ ለማረጋገጥ እየሰራን ነው'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም