ቡናችን የት ነው??

694
በምናሴ ያደሳ(ኢዜአ) ከአንድ ሺህ አመታት በፊት ቡናን ላገኙት ኢትዮጵያዊ አርሶአደርና ፊየሏ ምስጋና ይግባቸውና እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና የትውልድ ቦታ ተብላ በአለም ላይ ትታወቃለች :: እንደወለደችውና ለአለም እንዳስተዋወቀችው መጠን ግን ተጠቃሚ አልሆነችም ። ኢትዮጵያ ለአለም ያበረከተችው ብርቅዬ ሐብቷ ከጊዜ በኋላ በአረብ ነጋዴዎች ወደ አረብ አገር መሄዱን ያልተረዳው ዕውቁ ስዊዲናዊ ቦታኒስት ካሮሎስ ሊነስ በስህተት የዝርያውን ስም ኮፊ አረቢካ ብሎ መሰየሙ ቁጭት ቢፈጥርም የዝርያው መገኛ ኢትዮጵያ እንጂ አረብ አገር ያለመሆኑ በአለም አቀፍ ተመራማሪዎች ተረጋግጧል :: ቡና በኢትዮጵያ ከተገኘ ከረጅም አመታት በኋላ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጣዕሙ፣ በውስጡ በያዘው ካፌይን ፣ በምርታማነት መጠንና በሚለማበት አካባቢ በዋነኝነት ኮፊ አረቢካና ኮፊ ሮቡስታ በሚባሉ ሁለት ዝርያዎች ተከፍሎ እስከ ዛሬ ድረስ መጠሪያው ሆኖ ዘልቋል ። የአረቢካ ቡና ከሮቡስታ ቡና በሁሉም ረገድ ቀዳሚ ተመራጭና ተፈላጊ ሆኖ በአለም ላይ ስሙ ገኗል:: የአረቢካ ቡና ተመራጭ ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል ተፈጥሯዊ ጣዕሙና አነስተኛ የካፌይን መጠን መያዙ ይጠቀሳል:: ሆኖም ግን የአረቢካ ቡና በአመራረት ሂደቱ ከሮቡስታ ቡና ይበልጥ አድካሚ ነው ። ከተተከለ በኋላ ምርት የሚሰጠውም አራት አመታትን ጨርሶ ነው:: በአንፃሩ የሮቡስታ ቡና ከሁለት አመት በኋላ ምርት መስጠት ይጀምራል:: የአረቢካ ቡና በአለም ላይ ካለው የበለጠ ተመራጭነት የተነሳም በዋጋው ከሮቡስታ ቡና የበለጠ ነው:: ይህንን የቡና ምርት ከሚያመርቱ አገራት ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ናት:: በአለም ላይ ከብራዚል: ቬትናም: ኮሎምቢያና ኢንዶኔዥያ በመቀጠል አምስተኛዋ ቡና አቅራቢ የሆነችው ኢትዮጵያ እንደ ቡና መገኛነቷና የአየር ፀባይ ተስማሚነት አንፃር ያለችበት ደረጃ ብቻ ይገባት ነበር? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል ። የጥናት መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንደ ብራዚልና ቬትናም ያሉ አገራት ለልማቱ ያላቸውን ተስማሚ መሬት ጥቅም ላይ ሲያውሉ ኢትዮጵያ ግን አንድ ከመቶ ያህሉን እንኳ አልተጠቀመችበትም:: ከቡና ጋር  በቅርብ ጊዜ የተዋወቀችው ብራዚል በአሁኑ ወቅት በአመት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ያህል ቡና ለገበያ ታቀርባለች:: ቬትናምም ከ1.7 ሚሊዮን ቶን በላይ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ትከተላታለች:: በአንፃሩ የቡና እናት የሆነችው ኢትዮጵያ በየአመቱ ለገበያ የምታቀርበው ቡና ከ380 ሺህ ቶን የዘለለ  አይደለም:: ፕሮፌሰር አሊ መሐመድ በጅማ ዩኒቨርስቲ በመምህርነትና ተመራማሪነት ከ30 ዓመት በላይ አገልግለዋል:: ኢትዮጵያ በቡና ልማት ዘርፍ ከየትኛውም የአለም አገር የበለጠ ተስማሚ መሬትና የአየር ንብረት ቢኖራትም አልተጠቀመችበትም ይላሉ:: ሰሞኑን የመቱ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው የግብርና ምርምር ጉባኤ ላይም በመስኩ ምርታማነቱን በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን ያልተቻሉባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር አብራርተዋል:: በቀዳሚነት የጠቀሱትም በዘርፉ የምርምር ስራ የምሁራን ተሳትፎ አነስተኛ መሆንና ለቡና ኢንቨስትመንት የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆን ነው:: ፕሮፌሰር አሊ እንዳሉት በዓለም ላይ የቡና ምርት ፍላጎት በየአመቱ በ3ከመቶ እየጨመረ ቢሆንም የአቅርቦት መጠን እድገት ግን ከ1ነጥብ1 ከመቶ ያለፈ አይደለም:: ይህ ማለት በርካታ የአለም አገራት ቡና እየፈለጉ አቅራቢ አጥተዋል ማለት ነው:: ኢትዮጵያ ከ23 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለቡና ተስማሚ መሬት ቢኖራትም በአሁኑ ወቅት እየለማ ያለው ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር አይበልጥም:: በአንፃሩ እንደ ብራዚልና ቬትናም ያሉ አገራት ተስማሚ መሬታቸውን ሙሉ በሙሉ በቡና ሸፍነው ከአነስተኛ መሬት ብዙ ምርት ለመሰብሰብ ሰፊ የምርምር ተግባራት እያከናወኑ ነው:: ብራዚል የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከአንድ ሄክታር መሬት በአማካይ 1ነጥብ 4 ቶን ምርት እስከመሰብሰብ ደርሳለች:: በአንፃሩ በኢትዮጵያ ከአንድ ሄክታር መሬት የሚሰበሰበው ምርት ከ 0 ነጥብ 7 ቶን አይበልጥም:: ፕሮፌሰር አሊ ለምርታማነት ማነስ ምክንያቶችን ያብራራሉ ። በየጊዜው የተሻለ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣትና ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ረገድ የምሁራን ተሳትፎ እጅግ ያነሰ ነው:: ከዚህም ባለፈ የአየር ንብረት መዛባትን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን በማውጣት እንዲሁም ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በመስኖ ቡና ለማልማት የቴክኖሎጂ ሽግግር  ውሱንነት እንደ ችግር የሚነሳ ነው ይላሉ:: በቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመርና በማቀነባበር ለገበያ በማቅረብ በኩል ዕውቀትና ተነሳሽነቱ የጠፋውም በምርምር ዘርፍ የተቀናጀ ስራ አለመከናወኑ ይጠቅሳሉ ። "በአሁኑ ወቅት በቡና የምርምር ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘው የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል ብቻ ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ የምርምር መስኩን በተለያዩ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች ማስፋፋት ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ይመክራሉ:: የምርምር ተግባራት አነስተኛ ከመሆናቸው ባለፈም በተወሰነ መልኩ በምርምር የሚወጡት የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶአደሩ በማቅረብ ረገድ ውስንነት እንዳለ ነው የገለፁት:: ለምሳሌም በቅርብ ዓመታት በምርምር የተገኙና በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ 41 አይነት ምርጥ የቡና ዝርያዎች እስከ አሁን ድረስ አርሶአደሩ ጋር ያለ መድረሳቸውን ያነሳሉ:: በምሁራን ደረጃ ከምርምር ተሳታፊነት ማነስ በተጨማሪም አገሪቱ ለቡና ምርምር  የምትመድበው በጀት አነስተኛ መሆን አንዱ ችግር እንደሆነም ተናግረዋል:: በኢትዮጵያ ለዘርፉ ምርምር በየአመቱ የሚመደብ በጀት ከ300 ሺህ የአሜሪካ ዶላር አይበልጥም ያሉት ፕሮፌሰር አሊ በአንፃሩ ከኢትዮጵያ ባነሰ ደረጃ ቡና የምታመርተው ፊሊፒንስ በየአመቱ ከ10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በጀት እንደምትመድብ አብራርተዋል:: በቡና ምርት ግብይት ዘመናዊነት በኩል መንግስት ጅምር ተስፋ ሰጪ ተግባራት እያከናወነ ቢሆንም የአምራች አርሶአደሮችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል አሁንም ብዙ እንደሚቀር ተናግረዋል:: በኢትዮጵያ ተመርቶ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና የአምራቹ ተጠቃሚነት ከ60 ከመቶ እንደማይበልጥ ጠቁመዋል:: ቬትናም ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት ዋጋ የአምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት 98 ከመቶ መሆኑን በመግለፅ::የአምራቹን ቀጥታ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አርሶአደሩ በዩኒየኖችና ማህበራት በኩል ምርቱን በቀጥታ ለዓለም ገበያ የሚያቀርብበት አሰራር ሊመቻች ይገባልም ነው ያሉት:: የኦሮሚያ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዳይሬክተር ዶክተር ታሲሳ ከባ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ምርታማነት እንዳይቀንስና ጥራት እንዳይጓደል ምሁራን በግብርናው ምርምር በንቃት በመሳተፍ አዳዲስ አሰራሮችን ሊያፈልቁ ይገባል:: ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት እና በማላመድ የግብርና ልማቱን ለማዘመን ባለስልጣን መስርያ ቤቱ ከምርምር ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሆነ ነው የጠቀሱት:: የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እየተደረገ ባለው ጥረት የአየር ንብረት ለውጥና የአፈር መሸርሸር ዋነኞቹ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ልማቱን ለማፋጠን አዳዲስ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: የአለማችን ቁጥር አንድ ቡና አምራች አገር ብራዚል አሁን ላይ እያስጨነቃት ያለው ልማቱን ለማስፋፋት የተጋረጠባት የመሬት ችግር ነው ። ለቡና ልማት አመቺ የሆነውን አካባቢ በሙሉ በመስኖ ጭምር በማልማት ተጠቅማበታለችና::አሁን ላይ በቡና ክላስተር ትኩረት ሰጥታ እየሰራችበት ያለው እሴት በመጨመርና በማቀነባበር ለገበያ ማቅረብና በሄክታር ምርታማነትን ማሳደግ ነው:: ብራዚል ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በአመት 3.5 ሚሊዮን ቶን ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ ከ4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ እያገኘች ነው::በአንፃሩ ኢትዮጵያ ለቡና ልማት አመቺ ከሆነው 23ሚሊዮን የሚሆን መሬት እስካሁን ያለማችው ከአንድ ሚልዮን ሄክታር አይበልጥም:: በየአመቱ ለገበያ የምታቀርበው ምርትም ከ380 ሺህ ቶን ያነሰ ነው :: ከዚህ በመነሳት አንድ ነገር ማለት ይቻላል ። ኢትዮጵያ ለልማቱ አመቺ ከሆነው መሬቷ 10 ከመቶ ያህሉን እንኳን ብታለማ የአለም ገበያን በመቆጣጠር ኢኮኖሚዋን ማፈርጠም እንደምትችል ነው:: በኢትዮጵያ የሚለማው የቡና ዝርያ ደግሞ በአለም ላይ ቀዳሚ ተመራጭና የተሻለ ዋጋ የሚያወጣ የአረቢካ ቡና መሆኑን አገሪቱን የታደለች ያደርጋታል ። የአረቢካ ቡና ከሮቡስታ ቡና በተለየ ሞቃታማ ያልሆነና ከፍታ ባለው መሬት ላይ ስለሚለማ እንደ ቬትናም ያሉ አገራት የአረቢካ ቡናን ለማልማት ችግር ፈጥሮባቸዋል:: ምርታማነትን ማሳደግና ጥራትን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ  የተሻሻሉ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶአደሩ ማቅረብና ዘመናዊ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ነውና የዘርፉ ተመራማሪዎች በርቱልን እንላለን ::  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም