የኢንዱስትሪ ልማት መርሃ-ግብርን የሚደግፉ የመተግበሪያ ስትራቴጂዎች ስራ ላይ ሊውሉ ነው

109
ኢዜአ ህዳር 3/2012  ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት መርሃ-ግብርን የሚደግፉ የመተግበሪያ ስትራቴጂዎችን ስራ ላይ ለማዋል ዝግጅት ላይ መሆኗን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። አረንጓዴ ልማትና ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ሁኔታ ጋር የተላመዱ እንዲሆኑ የሚደግፉ የተለያዩ የመተግበሪያ ስልቶች ወጥተው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ ከአሜሪካ የደን ልማት አገልግሎት ከዓለም አቀፍ ፕሮግራም፣ ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ንዑስ ፕሮግራም ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ በመረቀቅ ላይ ባሉት ስትራቴጂዎች ዙሪያ መክረዋል። ውይይቱ በዋናነት የኢንዱስትሪና የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚያስከትለውን አካባቢያዊ ጉዳት ለመቀነስ ትኩረቱን ያደረገ ነው። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረኢየሱስ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የማምረቻና ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ ይገኛል። ዘርፉ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ውስጥም ያለው ድርሻ እንዲጎለብት የተለያዩ የማስፈፀሚያ መርሃ-ግብሮች እየተተገበሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የሚያስከትሉ የብክለት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ተጠቅሷል። ኢንዱስትሪዎች የሚያስከትሉትን ብክለት ለመከላከልና ለአካባቢው እና ለህብረተሰቡ ተስማሚ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ በመንግሥት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል። በዚህም በአገሪቱ ያሉትን ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ሁኔታ ጋር ተስማሚ አድርጎ ለመገንባት የሚያስችል የአምስት አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቀርጾ ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ስትራቴጂክ ዕቅዱ በዋናነት እያንዳንዱ ኢንዱስትሪ አካባቢውን በማይበክልና በማይጎዳ መልኩ መቋቋም እንደሚኖርበት ያስቀምጣል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የንጹህ ሃይል አማካሪ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሳደግ አካባቢንና ማህበረሰቡን በማይጎዳ መልኩ ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይም በአገሪቱ በዘርፉ ፖሊሲዎችን መቅረጽ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀምና መላመድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የአቅም ግንባታ ስራዎችና ስልጠናዎችን መስጠት እንዲሁ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል። ስትራቴጂክ ዕቅዱ በቀጣይ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም